ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ የመተማመን መንፈስን በማጎናፀፍ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞን እያፋጠነ ነው - አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ የመተማመን መንፈስን በማጎናፀፍ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞን እያፋጠነ ነው - አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ) ፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በራስ የመተማመን መንፈስን በማጎናጸፍ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞን እያፋጠነ መሆኑን የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) ገለጹ።
ኢትዮጵያውያን መሐንዲሶች፣ የገንዘብ ምንጮችና ግንበኞች ሆነው የገነቡት ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሚያዚያ 24 ቀን 2003 ዓ.ም በጉባ ተራሮች ግርጌ መሰረት መጣሉ ይታወሳል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ማስጀመሪያ ማግስትም ዓባይን ለሺህ ዓመታት በብቸኝነት ስትጠቀም የቆየችው ግብፅና አጋሮቿ ፕሮጀክቱን ለማደናቀፍ ጥረት አድርገዋል።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ለ14 ዓመታት ባደረጉት ተጋድሎ ዓባይ ለእናቱ በረከት የሚሆንበት ብስራት በጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተሰምቷል።
ዓባይ ተገርቶ የኤሌትሪክ ኃይል የማመንጨት ተግባሩንም ጀምራል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በምርቃቱ ወቅት የጎረቤት ሀገራት መሪዎችን፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ተቋማት ኃላፊዎችን ጋብዘው ታላቁ ሕዳሴ ግድብን ሲመርቁ ኢትዮጵያ በዓባይ ላይ ከውስጥ የተሻገረ የማንሰራራት ጅማሮን ማብሰራቸውም ይታወሳል።
ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን የማንሰራራት ጉዞ የሚያጎናጹፍ ግዙፍና አስተሳሳሪ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም ብቻ መገንባት እንደሚችሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በድል መጠናቀቅ ለዓለም ሕዝብ አሳይቷል።
ይህም ኢትዮጵያን የታዳሽ ኃይል አቅም በመገንባት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ አቅጣጫ ላይ ታሪክ ቀያሪ ድንቅ የልማት ውጤት ሆኖ በታሪክ ድርሳናት ተመዝግቧል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያውያን የራስ አቅም የተገነባ የመተባበር ውጤት ሆኖ የተመዘገበ ነው።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የነበራቸው ሁለንተናዊ ተሳትፎ በቀጣይም ያለአንዳች የውጭ እርዳታና ብድር ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም መገንባት እንደሚችሉ ትምህርት የሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሀገሪቱን በራስ የመተማመን መንፈስ ያነጸና የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞዋን እያፋጠነ የሚገኝ ግዙፍ አህጉራዊ የልማት ውጤት መሆኑንም አስረድተዋል።
ግድቡ ከብዙ ማዕዘናት ሲታይም የሀገሪቱን ዘመናዊ የልማት ጉዞ ወደ አዲስ ከፍታ በማሸጋገር አዲስ የመቻል መንፈስን ያጎናጸፈ ወሳኝ መሠረተ ልማት መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የሕዳሴው ግድብ ከኢትዮጵያ ባሻገር የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኃይል በማስተሳሰር በጋራና በትብብር የማደግ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ወሰን ተሻጋሪ የኤሌክትሪክ ኃይል መሠረተ ልማትም ኢትዮጵያ የጋራ ብልፅግናን በማሳለጥ ቀጣናዊና አህጉራዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለመፍጠር ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ ወሰን ተሻጋሪ ግዙፍ ወንዞቿን በማልማት የኢኮኖሚ ዕድገትን የሚያፋጥኑ ግዙፍ የኃይል ማመንጫና የመስኖ ግድቦችን መገንባት እንደሚጠበቅባት አስገንዝበዋል።
ለዚህም ሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የፈጠረላቸውን በራስ መተማመን በመጠቀም የኢኮኖሚ ዕድገትና ብልፅግናን ማፋጠን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።