የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ፤ የመጪው ዘመን የኢኮኖሚ ማንሰራራት መሰረት - ኢዜአ አማርኛ
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ፤ የመጪው ዘመን የኢኮኖሚ ማንሰራራት መሰረት
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ጉልህ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
ባለፉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ የተደረገው የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎም ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂም ሁሉን አቀፍ እና ሙሉ በሙሉ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የሚመራ ጠንካራ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያለመ ነው።
ይህም ፈጠራን፣ ምርምርን፣ ስታርት አፕን በማበረታታት፣ የሞባይልና ኢንተርኔት ተጠቃሚ ደንበኞች ቁጥር በመጨመር የፋይናንስ አካታችነትን ያረጋገጡ የቴሌብርና መሰል የዲጂታል ክፍያ አማራጮች ማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት አሠራር አካል የሚሆኑበትን ዕድል ፈጥሯል።
በፋይዳ ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያና መሶብ የአንድ ማዕከል የመንግሥት አገልግሎት መስጫ ማዕላትን በማበራከትም የተቀናጀ የመንግሥት አገልግሎት ምኅዳርን ፈጥሯል።
ይህም የተገልጋዮችን ምልልስ፣ ወጪ፣ ጉልበትና ጊዜ በመቆጠብ፣ የመንግሥት አገልግሎት ውጤታማነትን በማጎልበት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በማስፈን የኢትዮጵያን የብዝኅ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞ እያሳለጠ ይገኛል።
በአጠቃላይ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የፐብሊክ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ የሰው ኃይል አቅምና ፈጠራን በማጎልበት በሁሉም ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ማጠናቀቂያና «ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ባስጀመሩበት ወቅት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የኢትዮጵያን ብልፅግና ጉዞ የሚያፋጥን መሠረት መጣሉን አስታውሰዋል።
የስትራቴጂው ትግበራ ሙሉ በሙሉ በስኬት መጠናቀቁም ለቀጣይ የዲጂታል ኢትዮጵያ አስተማማኝ ግንባታ ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የትኩረት መስክ የብዝኅ ኢኮኖሚ ሥርዓትን በማሳለጥ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞ እያነጸ መሆኑን አብራርተዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂም በዜጎችና ተቋማት መካከል መተማመንን በማጎልበት ሁሉም ዜጋ አካታችና ፍትሐዊ የዲጂታል መሠረተ ልማት የሚያገኝበትን ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ለዚህም በስትራቴጂው መሠረት የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማት፣ የኢንተርኔት ተደራሽነት፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ የዲጂታል ገንዘብ ዝውውርና በተቋማት መካከል የዳታ ልውውጥ ውጤታማነት ለማሻሻል እንደሚሠራ ጠቅሰዋል።
የሰው ሠራሽ አስተውሎት፣ የሳይበር ደኅንነትና የዳታ አስተዳደር ላይ ትኩረት በማድረግ የወጣቶችን የቴክኖሎጂ ክህሎት ማሳደግ፣ አዳዲስ ፈጠራዎችን እና የዲጂታል ሥራ ዕድሎችን ማስፋፋት የስትራቴጂው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ዘመኑ የሚጠይቀው ጉዳይ በመሆኑ ኢትዮጵያ በዚህ መስክ ራሷን መቻል እንዳለባትም አስገንዝበዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የ100 ቀናት የመንግሥት ሥራ አፈጻጸም ግምገማን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን የትኩረት አቅጣጫ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ጉዞውን የሚቀርጽ እመርታዊ ለውጥ አምጥቷል ብለዋል።
በዚህም የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የፈጠራቸው የኢትዮ-ኮደርስ፣ የመሶብ አንድ ማዕከል፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያና የዲጂታል ፋይናንስ ግብይቶች ፈጠራን በማበረታታት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውን እያሳለጡ መሆናቸውን አንስተዋል።
በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ መሠረተ ልማት ዝርጋታ ጎን ለጎን የዜጎችን ዲጂታል ክህሎት ለማሳደግ እየተከናወኑ ከሚገኙ ሥራዎች መካከል የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና ተጠቃሽ ነው።
ወጣት ባዩሽ ተስፋዬና ቀለሙ ዘለቀ እንደገለጹት፤ ከመደበኛ ትምህርታቸው ጎን ለጎን የኮደርስ ሥልጠና መውሰዳቸው የዲጂታል ክህሎታቸውን በማበልጸግ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ወጣት መሰረት አቦሰጥ እንደምትለውም፤ የኢትዮ-ኮደርስ ሥልጠና የሰው ሠራሽ አስተውሎትና ዲጂታል ቴክኖሎጂ አቅሟን በማጎልበት ተጠቃሚ እያደረጋት ነው።
ወጣት እሸቱ አበራ በበኩሉ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና በሌሎች ቴክኖሎጂዎች በመታገዝ ዓይነ ሥውር ዜጎችም እንደ ማንኛውም ሰው የኮደርስ ሥልጠናን መውሰድና ተጠቃሚ በመሆን ከዘመኑ ጋር መራመድ እንደሚችሉ ዕድል መፍጠሩን ገልጿል።