ቀጥታ፡

ማዕከሉ እንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ ነው

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2018(ኢዜአ)፦መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በስፋት እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል ገለጸ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ሥር የሚገኘው የእንስሳት ልማትና ልህቀት ማዕከል፣ መጪውን በዓል ምክንያት በማድረግ የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረበ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሌክስ ደመቀ እንደገለጹት፤ ማዕከሉ አርሶ አደሮችን ለማቋቋም፣ የሥራ ዕድል ለመፍጠርና ገበያ ለማረጋጋት ነው የተቋቋመው፡፡ 

በአሁኑ ወቅት የደለቡ በሬዎችንና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በማዕከሉ እና በተለያዩ ቦታዎች በማቅረብ ላይ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጁ ባዛሮች ላይም ከ350 ሺህ በላይ እንቁላል ማቅረቡን ጠቅሰው ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በማዕከሉ የተሰማሩ አምራቾች በበኩላቸው መንግሥት ባመቻቸላቸው ዕድል ተጠቅመው ምርቶቻቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።  


 

የእንቁላል አምራች አበራሽ ንጉሤ እንዳሉትም ምርታቸውን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የወተት ተዋጽኦ አምራቿ ወይዘሮ የሺወርቅ ዳኛቸው ለበዓሉ የሚሆኑ እንደ ቅቤና አይብ ያሉ ምርቶችን ከውጭው ገበያ በቅናሽ ዋጋ ለህብረተሰቡ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

ማዕከሉ ከተቋቋመበት ከ2015 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በእንቁላል ጣይ ዶሮ እርባታ፣ በእንስሳት ማድለብና በወተት ላም እርባታ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም