ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ሚናውን እያጎለበተ የሚገኘው - የማዕድን ዘርፍ - ኢዜአ አማርኛ
ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ማንሰራራት ሚናውን እያጎለበተ የሚገኘው - የማዕድን ዘርፍ
አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 2/2018(ኢዜአ)፦መንግስት ለማዕድን ዘርፍ ልማት የሰጠው ልዩ ትኩረት እና እየተገኘ ያለው ውጤት ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱ ማንሰራራት የራሱን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በርካታ የማዕድን ሀብት ከሚገኝባቸው ሀገራት መካከል አንዷ ብትሆንም ቀደም ባሉት ጊዜያት ሀብቱን በማልማት ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ከማድረግ አንጻር አመርቂ አልነበረም።
ባለፉት ዓመታት መንግሥት በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም አጀንዳ ማዕድንን አንዱ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ልማት ምሰሶ በማድረጉ ዘርፉ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ምቹ ምህዳር ተፈጥሯል።
የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ ብርሃኔ ያዴሳ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመደመር መንግሥት በማዕድን ዘርፍ የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪው እንዲሰማሩ የፖሊሲ እና ምቹ ምህዳር መፍጠር ተችሏል።
የማዕድን ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ፣ ለተኪ ምርት ዕድገት እና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን በርካታ ፋይዳዎች እንዳለው አንስተው፤ ባለፉት አመታት ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
የውጭና የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን በስፋት በዘርፉ ማሰማራት የሚያስችሉ አጋዥ የማዕድን ፖሊሲና ህግጋት ተሻሽለው ለማጸደቅ በሂደት ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።
ቀደም ሲል ማዕድናት በጥሬው ወደ ውጭ ይላኩ እንደነበር አንስተው በአሁኑ ወቅት እሴት ጨምሮ ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ላይ ትኩረት መደረጉንም ገልጸዋል።
ለአብነትም በወርቅ፣ በድንጋይ ከሰል፣ ኦፓልና ሌሎች ጌጣጌጦች እሴት ተጨምሮባቸው ለውጭ ገበያ የሚቀርቡበት አሰራር በመፈጠሩ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በወርቅ ዘርፍ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ላይ ከፍተኛ ስኬት መገኘቱን አንስተው፤ የወርቅ ማጣሪያ በሀገር ውስጥ እንዲገነባ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመዋል።
የወርቅ ምርት በ2015 ዓ.ም ከነበረበት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን በ2018 ዓ.ም ወደ 44 ሚሊዮን ቶን ማደጉንና የውጭ ምንዛሬ ግኝቱም ከ196 ሚሊዮን ዶላር ወደ 5 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማደጉን ተናግረዋል፡፡
በሲሚንቶ ምርትም እንዲሁ ባለፉት አምስት ዓመታት ከ6 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቶን ወደ 10 ነጥብ 4 ሚሊዮን ቶን በማደግ ከፍተኛ እመርታ ማሳየቱን ገልጸዋል።
የድንጋይ ከሰል ምርት ቀደም ሲል በጥሬው ይቀርብ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ እሴት ተጨምሮበት ወጥ በሆነ ጥራት ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ግብዓት እስከ 75 በመቶ መሸፈን የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል ቀደም ሲል የሴራሚክ ምርት በአብዛኛው ከውጭ ይገባ እንደነበር አውስተው አሁን ላይ መንግስት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ በሀገር ውስጥ የማምረት አቅም አድጓል ብለዋል።
በዚህም በሴራሚክ ምርት የሀገር ውስጥ ፍላጎትን መሸፈንና ለግዥ ይወጣ የነበረን የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል።