በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ዕመርታዊ ለውጥ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ብስራት ነጋሪ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በግብርናው ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ዕመርታዊ ለውጥ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ብስራት ነጋሪ ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ በክልሎች ግብርናውን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የተጀመረው ጥረት የማንሰራራት ዘመን ብስራት ነጋሪ መሆኑን የተለያዩ ክልሎች የግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ገለጹ።
ኢትዮጵያ ግብርናውን በመካናይዜሽን፣ በኩታ ገጠም እርሻ፣ እንዲሁም ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ ግብዓቶችን በስፋት በማቅረብ በግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት ማሳደግ ችላለች።
የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘመንና እንደ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ዓይነት ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም እንደ ሀገር የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተያዘውን ግብ ማሳካት የሚያስችል ውጤት ተመዝግቧል።
ግብርናው ለኢኮኖሚያዊ ማንሰራራትና ለገጠር መዋቅራዊ ሽግግር ገንቢ ሚና መወጣት የሚችልበትን አቅም ፈጥሯል።
በኢትዮጵያ ግብርናውን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና ሁለንተናዊ ዕድገት ለማምጣት የተጀመረው ጥረት የማንሰራራት ዘመን ብስራት ነጋሪ ነው።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር ለኢዜአ እንዳሉት፤ መሬት፣ ጊዜ፣ ጉልበት እና ሀሳብን አቀናጅቶ በመጠቀም በሰብል ምርታማነት ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።
በዚህም በክልሉ በ2018 ወደ 1 ነጥብ 28 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን፤ አጠቃላይ የሰብል ምርት መጠኑን ከ161 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ የሰብል ብዝሃነትን በማስፋት ከውጭ የሚገባውን ምርት የሚተኩ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ማምረት መጀመራቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ማስረሻ በላቸው፤ በክልሉ "የማይታረስ መሬት ሊኖር አይገባም" በሚል በድግግሞሽ የሚታረሰውን መሬት ከ560 ሺህ ሄክታር ወደ 801 ሺህ ሄክታር በማሳደግ የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመነ ለማብሰር መሰረት የሚጥሉ ውጤቶች መመዝገባቸው ገልጸዋል።
በሆርቲካልቸር ልማት ከ41 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን በመግለጽ፤ ከ61 ሺህ ቶን በላይ ቡና ለዓለም ገበያ በማቅረብ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል።
በሌማት ትሩፋት ሥራዎችን ለማጠናከር የመኖ ማሽኖች ተከላ፣ የዓሳ ዕርባታ ማዕከላት ግንባታ፣ የዶሮ ማቆያና መሰል ማስፋፊዎችን እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የምክትል ቢሮ ኃላፊ አጀበ ስንሻው በበኩላቸው፤ በክልሉ የግብርና ሜካናይዜሽን በማስፋት 1 ነጥብ 4 ሚሊዬን ሄክታር መሬት በትራክተር ይታረሳል ብለዋል።
ለአርሶ አደሩ 7 ነጥብ 1 ሚሊዬን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እና ከ 310 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር በማቅረብ የአቅርቦትን ማሻሻልና የታቀደውን የግብርና ግብዓት ማሳካት መቻላቸውን ገልጸዋል።
በኩታ ገጠም እርሻ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማቅረብ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርበን ምርት ማሳደግ የሚያስችል ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።