ኢትዮጵያ የንጹህ ኃይል ልማቷን አጠናክራ ትቀጥላለች - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የንጹህ ኃይል ልማቷን አጠናክራ ትቀጥላለች - ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የንጹህ ኃይል ልማቷን አጠናክራ በመቀጠል ለጎረቤት ሀገራት የምታቀርበውን የኃይል መጠን ለማሳደግ እየሰራች መሆኑን ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ዱባይ እየተካሄደ ባለው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ (AIM Congress) ላይ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ ለታዳሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጉባኤው የዓለም ኢኮኖሚ መዋቅር በመሰረታዊነት እየተለወጠና የቴክኖሎጂ ለውጦች አጠቃላይ ሁኔታዎችን እየቀየረ ባለበት ጊዜ መካሄዱ ጠቃሚ ያደርገዋል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ተለዋዋጭ የጂኦ ፖለቲካ ሁኔታዎች የዓለምን የንግድ የእሴት ሰንሰለት እየወሰነ መምጣቱን ገልጸው፤ እነዚህ አዲስ ክስተቶች በማደግ ላይ ላሉ ሀገሮች በተለይም ለአፍሪካ ካመጡት ችግር ባልተናነሰ ወደ ውስጥ ለመመልከት ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰዋል።
ይህንንም ተከትሎ የአፍሪካ አገራት በአፍሪካ ኅብረት በኩል የዚህ ተለዋዋጭ ዓለም ክስተት ተመልካች ሳይሆኑ ዋነኛ ተሳታፊና ሥርዓት ገንቢ አካል ለመሆን የጋራ መግባባት መደረሱን ተናግረዋል።
በተለይም ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት እየተገበረቻቸው ያሉትን ተከታታይ የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሞች ከዚህ አኳያ የተቃኙ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ፕሬዝዳንት ታዬ እንደገለጹት፤ አፍሪካ ዘላቂነት ያለው ኢኮኖሚ እንድትገነባ ያላትን የስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ዕድሎች አሟጣ ለመጠቀም አምስት ዋና ዋና ጉዳዮችን ማከናወን ይጠበቅባታል።
አንደኛ በአፍሪካ የጋራ የኢንዱስትሪ ትራንስፎርሜሽን ለማምጣት በንጹህ የኤሌትሪክ ኃይል ማስፋፋት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ሀገሮች በተለይም ከንፋስ፣ ከፀሐይ፣ ከአንፋሎትና ከኃይድሮ ኤሌክትሪክ ልማት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም የንጹህ የኃይል አማራጭን እንደ ሀገራዊ ሃብት ብቻ ሳይሆን ለፈጣን የኢኮኖሚ እድገት መሰረት አድርጋ ትወስደዋለች ሲሉ ፕሬዝዳንቱ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከንጹህ ሃይል ብቻ 60 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት ገልጸው፤ እኤአ 2030 ኢትዮጵያ 13 ሺህ ሜጋ ዋት ለማመንጨት እቅድ እንዳላት ተናግረዋል።
በዚህም ለምስራቅ አፍሪካና ለሌሎች አገሮች የሚቀርበውን የኃይል አቅርቦት ለማሳደግ እንደምትሰራም ጠቁመዋል።
በሁለተኛ ደረጃ የአፍሪካ አገራት በግብርና ዘርፍ ላይ መሥራት እንዳለባቸው ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተለይም በስንዴ ምርት ዘርፍ ያስመዘገበችውን እመርታ በተሞክሮ ለታዳሚው አቅርበዋል።
በሦስተኛ ደረጃ የአፍሪካ አገሮች ከወርቅ ጀምሮ እስከ ኮባልትና ሊቲየም ድረስ ያላቸውን የተለያዩ የማዕድን ሀብቶች መጠቀም እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ታንታለም የተባለውን ማዕድን በማምረት በዓለም ስድስተኛ ደረጃ መያዟን ገልጸዋል።
የአፍሪካ አገሮች ለዘላቂና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት የመሰረተ ልማት ግንባታና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚሰራውን ሥራ ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋነኛ የትስስር ማዕከልነቷን ለማፅናት የሚያስችላትን የቢሾፍቱ አየር መንገድ በ12 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እየገነባች መሆኑን አስረድተዋል።
በሌላ በኩል ሦስት ነጥብ አራት ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ የአገራት አጠቃላይ አገራዊ ምርት የገበያ አቅም ያለው የአፍሪካ ነጸ የንግድ ቀጣና የመሰሉ ፕሮጀክቶች ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በአምስተኛ ደረጃ የአፍሪካ አገራት ያላቸውን የሰው ኃይል በአግባቡ ሊጠቀሙ እንደሚገባ አስገንዘበው፤ ኢትዮጵያ በተለይም በዲጂታል ቴክኖሎጂው ክህሎት ወጣቶች ያላቸውን አቅም ለማጎልበት የኮደር ሥልጠና እየሰጠች መሆኑን ጠቅሰዋል።
ለዚህ ኢኒሼቲቭ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው፤ ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል።
የተለያዩ የአገራት መሪዎች፣ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት ዛሬ በዱባይ የተጀመረው ዓመታዊው ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ጉባኤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መክሮ ከነገ በስትያ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።