ቀጥታ፡

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለበዓሉ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ትኩረት ተሰጥቷል

ሆሳዕና፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ):-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለዘመን መለወጫ በዓል የምርት አቅርቦትን በማሳደግ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪን ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ሀላፊ ባዩሽ ተስፋዬ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት በመጪው የዘመን መለወጫ በዓል ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የምርት አቅርቦት እንዲያድግ  ተደርጓል።

ለዚህም መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦትን በማሳደግ ህብረተሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምት ከማድረግ ባለፈ ህገ ወጥ ተግባራትን የሚቆጣጠር ግብረ ሀይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል።

ለእዚህም በክልሉ ከሚገኙ ምርት አቅራቢዎች፣ ዩኒየኖችና የሕብረት ሥራ ማህበራት ጋር በቅንጅት በመስራት በመደበኛና በተዘጋጁ ጊዜያዊ የግብይት ማዕከላት ምርት በበቂ ሁኔታ መቅረቡን ተናግረዋል።

በዚህም ማህበረሰቡ ለበዓሉ የሚፈልጋቸውን የፍጆታ ምርቶች በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

ቢሮው ለዘመን መለወጫ በዓል ከ395 ሺህ ሊትር በላይ ዘይት እና ከ7 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል እንዲቀርብ ማድረጉንም ባዩሽ (ዶ/ር) አክለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ለበዓሉ ጤፍ፣ ስንዴና የቁም እንስሳትን በስፋትና በጥራት ለማህበረሰቡ እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል::

በዓሉን ምክንያት በማድረግ የሚፈጸም ህገ ወጥነትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ማህበረሰቡ መረጃ በመስጠት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም አስገንዝበዋል።


 

የሆሳዕና ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ታሪኬ ግርማ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል የበዓል ወቅትን ምክንያት በማድረግ ይስተዋል የነበረው የዋጋ ጭማሪ አስካሁን አለመኖሩን ተናግረዋል።

ለዘመን መለወጫ በዓል የሚሆናቸውን ዶሮ፣ ሽንኩርትና ሌሎች አስፈላጊ ግብዓቶችን መሸመታቸውንም ተናግረዋል።

በተለይም በምርት አቅርቦቱ ላይ የተሻለ ሥራ በመሰራቱ  አማርጠው ለመግዛት ምቹ ሁኔታ እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል።


 

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ኢዮሲያስ ቀጭኔ በበኩላቸው ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል የሚሆን በሬ ለመግዛት ወደገበያው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በገበያው በሬን ጨምሮ የቁም እንስሳት በስፋት መቅረባቸውን ገልጸው፣ በአቅማቸውና በተመጣጣኝ ዋጋ የእርድ በሬ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም