ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል የልማት አቅሞችን ወደ ውጤት በመቀየር ዘላቂ እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል

ጋምቤላ ፤ጳጉሜን 2 /2018 (ኢዜአ)፡-በጋምቤላ ክልል  የመልማት አቅሞችን  ወደ ውጤት በመቀየር  ዘላቂ  እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር  ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር) ገለጹ።

ጳጉሜ 2 የማንሰራራት ቀን ’’ዘላቂ ልማት ለሀገራዊ ማንሰራራት’’ በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተከብሯል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋትሉዋክ ሮን (ዶ/ር)  በወቅቱ እንዳሉት የክልሉን  የተፈጥሮ ሀብቶችና  የሰው ሀይልን በማቀናጀት  ዘላቂ  እድገት ለማስመዝገብ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል።

በክልሉ  የተከናወኑ  የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት፣ የቱሪዝም፣ የግብርና እና ሌሎች መስኮች  የህዝቡን ተጠቃሚነት  ከማረጋገጥ ባለፈ በሀገራዊ ማንሰራራት ውስጥ ድርሻ አላቸው ብለዋል። 

በቀጣይም እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ያሉትን የመልማት አቅሞች በመጠቀም የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞና የኢትዮጵያን ከፍታ እውን ለማድረግ ይበልጥ  የምንተጋበት ጊዜ ነው ብለዋል።


 

በተለይም በክልሉ ያሉትን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብቶችና የመልማት እድሎችን በመጠቀም የክልሉን ልማትና እድገት ለማፋጠን ከመቸውም ጊዜ በበለጠ በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ማክበዲ ኡቻን በበኩላቸው እንዳሉት ዛሬ የምናስበው የኢትዮጵያ የማንሰራራት ቀን የገጠሙንን ፈተናዎች በጽናት ተቋቁመን፤ በህብረትና በጋራ ጥረት ወደ ላቀ ከፍታ የተሻገርንበት ምዕራፍ ነው ብለዋል።


 

 በክልሉ ያሉትን ጸጋዎች በማልማት የህዝቡን ህይወት ለመለወጥ ይበልጥ ጠንክረን  እንሰራለን  ሲሉም ተናግረዋል።

በጋምቤላ ከተማ አደባባይ በተከበረው የጳጉሜ 2 የማንሰራራት ቀን ላይ የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችን ጨምሮ የከተማው ነዋሪዎች ተገኝተዋል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም