ቀጥታ፡

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ መፍትሔ በመቀየስ ረገድ መሪ ሚና መጫወት ይገባታል-ክላቨር ጋቴቴ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ አፍሪካ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ድርድሮችና መፍትሔዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የጎላ ሚና መጫወት እንዳለባት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ፡፡

14ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ እና ልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው። ጉባኤው "ከተስፋ ቃል ወደ ተግባር፤ የቤሌም-አንታልያ-አዲስ አበባ ፍኖተ ካርታ" በሚል መሪ ሐሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክላቨር ጋቴቴ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፣ አፍሪካ ለዓለም አቀፍ የካርቦን ልቀት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አራት በመቶ ቢሆንም የችግሩን ከባድ መዘዝ እየተሸከመች ትገኛለች።

ሆኖም ይህ እውነታ ለአፍሪካ የተጎጂነት ታሪክ ብቻ ሆኖ ሊቀጥል እንደማይገባ ተናግረው አፍሪካ ያላትን ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል አቅም፣ የማዕድን ሀብቶች፣ ወጣት የሰው ኃይል እና እያደገ ያለውን ገበያ በመጠቀም በዓለም አቀፍ ደረጃ መፍትሔዎችን በመቀየስ ረገድ መሪ ሚና መጫወት እንዳለባት ገልጸዋል።

አፍሪካ እስከ እ.ኤ.አ 2030 ድረስ የተቀመጡ የአየር ንብረት ግቦችን ለመተግበር በየዓመቱ 277 ቢሊዮን ዶላር የሚያስፈልጋት ቢሆንም እያገኘች ያለችው ከፍላጎቷ 11 በመቶ ያህሉን ብቻ ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት እርምጃዎች ከኃይል ተደራሽነት፣ከኢንዱስትሪ ልማት እና ከሥራ እድል ፈጠራ ጋር ተያይዘው መከናወን እንዳለባቸው አሳስበዋል። ከ600 ሚሊዮን በላይ አፍሪካውያን አሁንም የኤሌክትሪክ አገልግሎት ያላገኙ በመሆናቸው የታዳሽ ኃይልን ማስፋፋት የኢኮኖሚው መሠረት ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናን በመጠቀም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ሀብቶች ላይ እሴት በመጨመር አህጉራዊ የእሴት ሰንሰለት መገንባት ይቻላል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም