ቀጥታ፡

ከሀገራዊ ምክክሩ የተገኙ ምክረ-ሃሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይቀርባሉ

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ ከሀገራዊ ምክክሩ የተገኙ ምክረ-ሃሳቦች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ ምክር ቤቱ ገልጿል።

ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ- ሃሳቦች በየፈርጁ እየተደራጁ መሆኑንና በቀጣይ ምክረ-ሃሳቦቹን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚያቀርብ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

የኮሚሽኑ መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፦

ኮሚሽኑ ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችን በየፈርጁ በማደራጀት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 01 ቀን - ነሐሴ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤውን ሲያስተባብር መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ በርካታ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸውን ምክረ-ሃሳቦች ማሰባሰብ የቻለ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ለመመካከር ያሳዩት ቁርጠኝነት ውጤት ነው፡፡

ኮሚሽኑ በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 አንቀፅ 9 (10፣ 11፣ 12) በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት

👉የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ- ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልጽ ሰነድ በማዘጋጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለአስፈጻሚ አካሉ እና ለሌሎች የሚመለከታቸዉ የመንግስት አካላት አቅርቦ፤ ለሕዝብም ይፋ እንደሚያደርግ፤

👉 መንግሥት ከሀገራዊ ውይይቶች የሚገኙ ምክረ-ሃሳቦችን በተግባር ላይ ለማዋል እንዲችል ግልፅ እና ተጨባጭ የሆነ ዕቅድ እንዲዘጋጅ አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ፤ እንዲሁም

👉 የምክረ-ሃሳቦቹን አፈፃፀም መከታተል የሚያስችል ሥርዓት እንደሚዘረጋ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

ይህንን መነሻ በማድረግ ኮሚሽኑ፦

👉በአሁኑ ሰዓት ከሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የተገኙ ምክረ-ሃሳቦችን በየፈርጁ በማደራጀት ላይ ይገኛል፤

👉በቀጣይ ምክረ-ሃሳቦቹን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀርባል፤

👉በመቀጠልም ምክረ-ሃሳቦቹን አግባብነት ባለው መንገድ ለሕዝብ ይፋ ያደርጋል፤

👉በመጨረሻም ምክረ-ሃሳቦቹን ለአስፈፃሚ በማቅረብ ተፈፃሚነታቸውን ይከታተላል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም