በኃይል ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኃይል ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ ባለፉት ስምንት ዓመታት በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ በእጅጉ የሚያፋጥኑ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
ኢዜአ፣ በኢትዮጵያ ባለፉት ስምንት ዓመታት የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም መሰረተ ልማቶችን ለማጠናከር በተከናወኑ ተግባራት የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻን አነጋግሯል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት፣ የለውጡ ዓመታት የኢትዮጵያን ኃይል የማመንጨት አቅም በማሳደግ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን እውን የሚያደርጉ ዘርፈ ብዙ ስራዎች የተከናወኑባቸው ናቸው።
የኃይል ማስተላለፍ አቅም ማሳደግ የተቻለው እንዲሁም ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ግንኙነት ይበልጥ ማጠናከር መቻሉን ጠቁመው ለማሳያነትም ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር የፈጸመችውን የኃይል ሽያጭ ስምምነት ማንሳት እንደሚቻል አብራርተዋል።
የአሰላ ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተጠናቆ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ እንዲሁም የዓይሻ ንፋስ ኃይል ማመንጫ በከፊል ተጠናቅቆ ለምርቃት መብቃቱንም ጠቅሰዋል፡፡
በአጠቃላይ ባለፉት ስምንት ዓመታት በኤሌክትሪክ ኃይል ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች የኢትዮጵያን የማንሰራራት ጉዞ ያረጋገጡ ናቸው ሲሉ ኢንጂነር አሸብር ገልጸዋል።
የሀገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ወደ 9ሺህ 730 ሜጋ ዋት ማሳደግ መቻሉንም ተናግረዋል።
ተቋሙ በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 39 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ያገኘበት፣ ከ33ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኢነርጂ በማመንጨትም ለተጠቃሚዎች ማድረስ የቻለበት እንደሆነ አብራርተዋል።
በኢነርጂ መስክ ለተመዘገቡት ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት መካከል የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
ግድቡ ኢትዮጵያ የኢነርጂ የማመንጨት አቅሟን በእጥፍ ያሳደገ፣ ከኃይል ማመንጨት በላይ ትርጉም ያለው ግዙፍ ሀብታችን ነው ብለዋል።
ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚገኘው ኢነርጂ በዘርፉ የምናገኘውን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ፣ ለሌሎች ፕሮጀክቶች መሳለጥ አቅም መሆኑን አንስተዋል።
2018 በጀት ዓመትን የማንሰራራት ዓመት በማለት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገባቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ይህ አካሄድ በቀጣይ ዓመት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
የኃይል አቅርቦትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የኮይሻ ግድብ ፕሮጀክት ግንባታን ማጠናቀቅ፣ እንዲሁም የዓይሻ ንፋስ ኃይል ፕሮጀክት ሁለተኛ ፌዝን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ተጨማሪ 40 ሜጋ ዋት ወደ ሲስተም እንዲገባ ማድረግ፣ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ካቀዳቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የፕሮጀክቶችን ግንባታ ማፋጠን፣ እንዲሁም ከፀሐይ፣ ከንፋስ እና ከሌሎች ምንጮች ኃይል ለማመንጨት የሚያስችሉ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ወደ ተግባር ማስገባት ከታቀዱ ተግባራት መካከል መሆናቸውን አስታውቀዋል።