ቀጥታ፡

የማንሰራራት ቀንን ምክንያት በማድረግ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአዲስ አበባ ከተማ የማንሰራራት ቀንን ምክንያት በማድረግ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ የከንቲባ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የአዲስ አመት መቀበያ የሆነችው ጳጉሜን ቀናት በተለያየ ስያሜዎች እየተከበሩ ሲሆን የዛሬው ጳጉሜን 2 ደግሞ በማንሰራራት ተሰይሟል።

የአዲስ አበባ የማንሰራራት ማሳያ የሆነው የትራንስፖርት ዘርፍም ለከተማዋ ነዋሪዎች ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ቀኑን እያከበረ መሆኑም ተገልጿል።

ለግማሽ ቀን በሚቆየው ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የከተማ አውቶብስና የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ለደንበኞቻቸው መልካም የአዲስ አመት በመመኘት ጭምር እየተሳተፉ መሆናቸውም እንዲሁ።

በቦሌ ሚሊኒየም አካባቢ የተሰጠውን ነጻ የትራንስፖርት አገልግሎት ያስጀመሩት የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳኛቸው ሽፈራው እንዳሉት በነጻ ትራንስፖርቱ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን የመዲናዋ ነዋሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

የአዲስ አበባ የማንሰራራት ማሳያ ከሆኑ ልማቶች መካከልም የትራንስፖርት ዘርፉ ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰው፤ የከተማዋን እድገት የሚመጠን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስፋፋት ዘርፉ ማንሰራራት መቻሉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም