ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል በግብርናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል

ሀዋሳ፣ ‎ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል በግብርናው ዘርፍ በተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ገለጸ።

የሲዳማ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ያለፉት አምስት ዓመታት የዘርፉ አፈጻጸምና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የሴክተር ጉባኤ ተካሂዷል። 


 

በጉባኤው ላይ የተገኙት የሲዳማ ክልል የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ አስፋው ጎኔሶ በክልሉ በግብርናው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ለውጥ ማምጣታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ባለፉት ዓመታት የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂና አሰራሮች በመጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ማሳደግ ተችሏል ብለዋል።

በተለይ ህዝብን በማነቃነቅ የማይታረሱ መሬቶች ጭምር እንዲታረሱ ማድረግና አርሶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በመስኖ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤቶች  መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በመስኖ የሚለማ መሬት መጠን በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ገልጸው፣ አርሶ አደሩ በዓመት ከሦስት ጊዜ በላይ በማምረት ከራሱ ባለፈ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መምሩ ሞኬ በበኩላቸው እንዳሉት በዘርፉ የ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ ተቀርፆ ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡

በዚህም የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ፣ ገበያ ተኮር እና ለኢንዱስትሪዎች ግብዐት የሚሆኑ ምርቶችን በስፋት የማምረትና በእሴት ሰንለት ውስጥ ሰፊ የሥራ ዕድል የመፍጠር ግቦች ተነድፈው በርካታ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

እነዚህን ግቦች ከማሳካት አንፃርም የተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ለውጥ እያሳዩ መምጣታቸውን አስረድተዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በቆሎ፣ ገብስ፣ ስንዴና ጤፍን ጨምሮ በሲዳማ ክልል በዋና ዋና ሰብሎች ብቻ የማሳ ሽፋን ከነበረበት 70 ሺህ ሄክታር ወደ 123 ሺህ ሄክታር ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል።

በቡና ልማትም የተመረጡ ዝርያዎችን በማስፋትና መሰል ሥራዎችን በማከናወን ከአምስት ዓመት በፊት ከነበረበት 149 ሺህ ሄክታር ሽፋን አሁን ላይ 186 ሺህ ሄክታር ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በሞዴል አርሶ አደሮች ደረጃ ያለውን የቡና ምርታማነት እድገት ወደ ሁሉም አርሶ አደሮች ለማስፋት በቀጣይ በትኩረት ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም