አዲስ አበባ ከተማን የአፍሪካ የፅዳትና ውበት ተምሳሌት የሚያደርጉ እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል - ኢዜአ አማርኛ
አዲስ አበባ ከተማን የአፍሪካ የፅዳትና ውበት ተምሳሌት የሚያደርጉ እመርታዊ ለውጦች ተመዝግበዋል
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ከተማን በአፍሪካ የፅዳትና ውበት ተምሳሌት የሚያደርጉ እመርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን የከተማዋ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር ገለፁ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ገጽታ ለመቀየርና ጽዳቷን ለመጠበቅ ያለመ ከተማ አቀፍ የጽዳት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በዛሬው ዕለት በልደታ ክፍለ ከተማ በይፋ አስጀምሯል።
የከተማዋ ከፍተኛ አመራሮች፣ የጽዳት አምባሳደሮች፣ አርቲስቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና የጸጥታ አካላት በከተማ አቀፍ የጽዳት ንቅናቄ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሳዲቅ ሽኩር እንዳሉት፣ አዲስ አበባን ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ ሁሉንም ሕብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ንቅናቄ መፍጠር ያስፈልጋል።
ጷጉሜን 1 "የእምርታ ቀን" የከተማዋን የጽዳትና ውበት ስኬቶች በማስቀጠል የጽዳትን ባህል ለማዳበር ራሳችንን የምናድስበት ነው ብለዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የከተማዋን ገጽታ ለማሻሻል፣ የኢኮኖሚ እድገትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስረድተዋል።
ከተማዋ "ለአፍሪካ መዲናነት አትመጥንም" ከሚል ስም ተላቃ፣ ዛሬ ላይ በአፍሪካ የጽዳትና ውበት ተምሳሌት ለመሆን መብቃቷ እንደ ትልቅ እመርታ እና ስኬት የሚታወስበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።
የጽዳትና ውበት ሥራዎችን በመንግሥት ደረጃ ብቻ ማስቀጠል ስለማይቻል ሕብረተሰቡና ባለድርሻ አካላት በቀጥታ ባለቤት እንዲሆኑም አሳስበዋል።
ይህ ከተማ አቀፍ የጽዳት ንቅናቄ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች በተቀናጀ መልኩ እንደሚቀጥል ገልጸው፤ ሕብረተሰቡም መኖሪያና ሥራ አካባቢውን በመጠበቅ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ጽዳት አምባሳደር እና የአገልግሎት አሰጣጥ የምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን ፀሃይ በበኩሉ፤ አዲሱን ዓመት አካባቢን በጽዳት እንቅስቃሴዎች መጀመር የሚያበረታታ እና በጎ ምልከታን የሚፈጥር ተግባር ነው ብለዋል።
ዘላቂ የሆነ የጽዳት እንቅስቃሴ ለማድረግ ማህበረሰቡን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ ንቅናቄ መፍጠሩ፣ የህብረት እና የጥንካሬ ማሳያ እንደሆነ ገልጸዋል።
የጽዳት አምባሳደር አርቲስት ሙሉነህ ዘለቀ በበኩላቸው፤ ባለፉት ዓመታት በህዝብና በመንግሥት ቅንጅት ከተማዋን በመለወጥ ረገድ ከፍተኛ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ለውጥ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይወሰን በሌሎች የሀገሪቷ ክልሎችና ከተሞችም እየተስፋፋ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የጽዳት አምባሳደር አርቲስት ኤልያስ ተባባል በሰጡት አስተያየት፣ አዲስ አበባ የአፍሪካ ዋና ከተማ በመሆኗ ሁልጊዜ ጽዱ እና ንጹህ መሆን አለባት ብለዋል።
የጽዳት አምባሳደር ኮሜዲያን ማርቆስ ፍቅሩ፣ የጽዳት ሥራ የአንድ ወቅት እንቅስቃሴ ሳይሆን ሁልጊዜ በየቀኑ በየአካባቢው ሊከናወን የሚገባ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በጽዳት ዘመቻው በመሳተፏ የተሰማትን ደስታ የገለጸች ሰርካለም ተፈራ እንደተናገረችው፤ የጽዳት እንቅስቃሴው ለከተማዋ ነዋሪዎች በርካታ ጥቅሞች አሉት።