በባሌ ዞን የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ይጠናከራሉ
አጋርፋ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፡-በባሌ ዞን የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
በዞኑ የጳጉሜን-1 "የእመርታ ቀን"ን በማስመልከት "እመርታ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው የግብርና ልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ በአጋርፋ ወረዳ ተካሂዷል።
በዞኑ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተሰሩት ሥራዎች እመርታዊ ለውጦች መታየታቸውም ተመልክቷል።
በመርሃግብሩ ላይ የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ ከተረጂነት ለመውጣትና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ተግባራዊ የተደረጉ ኢንሼቲቮች ውጤት እያስመዘገቡ ነው።
በተለይ የኩታገጠም አሰራር፣ ምርጥ ዘር አጠቃቀምና ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮች በስፋት እየተተገበሩ መምጣት የእመርታዊ ለውጡ ማሳያዎች መሆናቸውን አክለዋል።
አቶ አልይ እንዳሉት በዞኑ በ2018/2019 የምርት ዘመን ከ580 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የዞኑ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አፍራሳ እንዳሉት በዞኑ ባለፉት ዓመታት የግብርና ሜካናይዜሽን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ይጠናከራሉ።
በተለይ የኩታገጠም አሰራርን ማስፋት፣ የሰብል ምርትን ማሳደግ፣ የበጋ መስኖን ልማትን ማጠናከርና ዘመናዊ የእንስሳት እርባታን ማስፋፋት አበረታች ውጤት ማምጣቱን ገልጸዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት የግብርና ሜካናይዜሽንና ዘመናዊ የግብርና አሰራርን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አቶ ብርሀኑ አስታውቀዋል።
የአጋርፋ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አደም ከድር በሰጡት አስተያየት በ 2 ሄክታር መሬታቸው ላይ በኩታገጠም እያለሙ ካለው የስንዴ ልማት የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።