ቀጥታ፡

የስንዴ አብዮት፦ የኢትዮጵያ ማንሰራራት አብነት

ኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ፍላጎቷ ከ107 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ነው። ይህንን ፍላጎት ለማሟላት ለዓመታት ከ700 ሚሊዮን ዶላር እስከ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ውድ የውጭ ምንዛሬ ለስንዴ ግዢ ስታወጣ ቆይታለች።

ከዚህ ቀደም ሀገሪቱ ከዓመታዊ ፍላጎቷ መሸፈን የምትችለው ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚሆነውን ብቻ ሲሆን፣ ቀሪውን በውጭ ግዢ ትሸፍን ነበር።

በተለይም የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት በዓለም አቀፍ ደረጃ 30 በመቶ የሚሆነውን የስንዴ አቅርቦት በማወኩ ኢትዮጵያ ከባድ የአቅርቦት ፈተና ውስጥ እንድትገባ አድርጓት ነበር።

ይህንን የረጅም ጊዜ ተግዳሮት በዘላቂነት ለመቅረፍ መንግሥት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን በስፋት በመተግበር፣አሲዳማ መሬቶችን በኖራ በማከም እና ረግረጋማ ቦታዎችን በቴክኖሎጂ በማድረቅ ታሪካዊ ለውጥ ለማምጣት እርምጃዎችን ወስዷል።

በኩታ ገጠም እርሻና በዘመናዊ ማሽነሪዎች አጠቃቀም የታጀበው ይህ የልማት አብዮት ፍሬ አፍርቶ፣ ኢትዮጵያ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ ከውጭ የምታስገባውን የንግድ ስንዴ ሙሉ በሙሉ አቁማለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በስንዴ ልማት የተመዘገበው ስኬት ከውጭ ማስገባትን ማቆም ላይ ብቻ ሳይወሰን፣ ሀገሪቱ ወደ ውጭ መላክ (ኤክስፖርት ማድረግ) የሚያስችል አቅም እንዳላት ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።

በዚህም መሠረት የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ባሌ ዞን በይፋ የስንዴ ኤክስፖርት የተጀመረ ሲሆን፣ ለዚህ ስኬታማነት የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል።

ብሔራዊ የማክሮ ኢኮኖሚና የኤክስፖርት ኮሚቴ ሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ፍጆታዋን ሸፍና 32 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚያስችል አቅም እንዳላት አረጋግጦ፣የ2.9 ሚሊዮን ኩንታል የውል ስምምነቶች ከረድኤትና ከሀገር ውስጥ ድርጅቶች ጋር ተፈራርሟል።

ከሀገር ውስጥ አቅርቦት ባሻገር ኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም ለኬንያ ስንዴ ለመላክ ስምምነት የፈረመች ሲሆን፣ ጅቡቲም ከኢትዮጵያ ስንዴ መግዛት እንደምትፈልግ ገልጻ ከኢትዮጵያ የስንዴ ልማት ብዙ ተሞክሮ እንደምትወስድ አመላክታለች።

የአፍሪካ ልማት ባንክ ስንዴ ከውጭ እንደማታስገባ እና ምርቷን ለጎረቤት ሀገራት ማስተላለፍ መጀመሯን በማድነቅ ለአህጉሪቱ እንደ ትልቅ የዕድገት ተሞክሮ አቅርቧል።

የአሜሪካ የውጭ ግብርና ቢሮ ሪፖርቶችም በኢትዮጵያ የስንዴ ምርት ዘርፍ ትልቅ እመርታ እያሳየ መምጣቱን ጠቅሰው፣መንግሥት የመስኖ ልማትና የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ በማጠናከሩ ሀገሪቱ ከፍተኛ ምርት ማምረቷን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ290 እስከ 340 ሚሊዮን ኩንታል (ከ29 እስከ 34 ሚሊዮን ቶን) በላይ መድረሱ ኢትዮጵያን በአፍሪካ አህጉር ቀዳሚ የስንዴ አምራች ሀገር አድርጓታል።

የስንዴ ልማቱ አርሶ አደሩን ከቀድሞው ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ አላቆ፣ በኩታ ገጠም እርሻና በሜካናይዜሽን ታግዞ ወደ ሰፋፊ የንግድ ምርት እንዲገባ አስችሏል።

የተሻሻሉ የስንዴ የሰብል ዝርያዎች መለቀቃቸው ለዚህ ውጤት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን፣ የምርት አቅርቦት ሰንሰለቱን ማዘመን በቀጣይነት በትኩረት እየተሠራበት ይገኛል።

በምርት አቅም እና በኩታ ገጠም እርሻ የተመዘገቡት እነዚህ ሰፊ ስኬቶች፣ ሀገሪቱ በኢኮኖሚ አቅም እያደረገችው ያለውን ሁለገብ ማንሰራራት በግልጽ የሚያሳዩ አብነቶች ናቸው።

ይህ ትልቅ ለውጥ ኢትዮጵያ ከድህነትና ከዕርዳታ ጥገኝነት ወጥታ የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራትም ተስፋ የሚሰጥ አህጉራዊ አርዓያ መሆን መቻሏን አስመስክሯል።

ይህ የምርት እመርታ በግብርናው ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ የሀገሪቱን ማንሰራራት የሚያረጋግጥ ትልቅ ምዕራፍ ነው።

ለዘመናት በውጭ ዕርዳታና በለጋሾች ላይ ተወሰና የነበረችው ኢትዮጵያ፣ዛሬ በራሷ አቅም በመሥራት አህጉራዊ አርዓያ መሆን መቻሏ ትልቅ ስኬት ነው።

የኢኮኖሚ ነፃነት እና የሉዓላዊነት ማዕቀፍን በማረጋገጥ ረገድም የስንዴ አብዮቱ የሀገርን አቅም የሚያሳይ ተምሳሌት ሆኗል።

በመሆኑም በስንዴ ልማት የተገኘው ይህ ድል የግብርና ዘርፍ ስኬት ብቻ አይደለም፤ ኢትዮጵያውያን በቁርጠኝነትና በትጋት ከሠሩ ሀገርን ማሻገር እንደሚችሉ በተግባር ያረጋገጡበት ታላቅ የሀገር የማንሰራራት ማሳያ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም