ቀጥታ፡

ኢትዮ ቴሌኮም በአፋር ክልል ለትምህርት ሥራ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ ነው

ሰመራ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፡-ኢትዮ-ቴሌኮም በአፋር ክልል ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ለትምህርት ሥራ ስኬታማነት የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ ገለጸ።

ኢትዮ ቴሌኮም በሠመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር አሰቦዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ድጋፍ ለሚሹ ተማሪዎች ዛሬ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ  አድርጓል።

በርክክቡ መርሃ ግብሩ ላይ የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኀላፊ ሙሳ አደም እንዳሉት ኢትዮ ቴሌኮም ለተማሪዎች ያደረገው ድጋፍ በክልሉ  የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ተደማሪ አቅም አለው።


 

ዛሬ የተደረገው የመማሪያ ቁሳቅስ ድጋፍ ከ4 ሺህ በላይ ተማሪዎችን የትምህርት ቁሳቁስ ፍላጎት በመሸፈን ለትምህርት ስራ ስኬታማነት አዎንታዊ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

በኢትዮ ቴሌኮም የሰሜን ምስራቅ ምስራቅ ሪጅን ዋና ዳይሬክተር አቶ ብርሃነ ፍፁም ኢትዮ ቴሌኮም ከመደበኛ ስራው በተጓዳኝ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በመወጣት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የትምህርት ግብአትን ማቅረቡን ተናግረዋል።

ድጋፉ ለትምህርት ሥራ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸው፣ ለድጋፉ ከ2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና በቀጣይም ተመሳሳይ ተግባራት እንደሚጠናከሩ ተናግረዋል።

የአሰቦዳ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር መሀመድ ገዶ በበኩላቸው፣ በትምህርቱ ቤቱ ድጋፍ ለሚያሻቸው ተማሪዎች የተደረገው ድጋፍ የወላጆችን ችግር የሚያቃልል መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለት የተደረገላቸው  የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ  በትምህርታቸው  ጠንክረው ለመማር ተነሳሽነት መፍጠሩን  የገለፁት ደግሞ ተማሪ ፋጡማ መሐመድ እና ተማሪ መሐመድ አህመድ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም