መሶብ የአንድ ማዕከል፤ የመደመር መንግሥት የአገልግሎት ትራንስፎርሜሽን ማስፈንጠሪያ - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል፤ የመደመር መንግሥት የአገልግሎት ትራንስፎርሜሽን ማስፈንጠሪያ
መሶብ የአንድ ማዕከል፤ የመደመር መንግሥት የአገልግሎት ትራንስፎርሜሽን ማስፈንጠሪያ
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነት የተጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፣ የዜጎችን እንግልት በመቀነስና የመንግሥት አሰራርን በማዘመን ረገድ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ ይገኛል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመንግሥት አሰራርን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን፣ የወረቀት ስራንና እንግልትን በማስቀረት ቀልጣፋ፣ ፍትሃዊና ግልጽ አገልግሎት ለመስጠት የተዘረጋ ስርዓት ነው።
ፕሮጀክቱ አገልግሎት ፈላጊዎች በአንድ ማዕከል በርካታ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ታሳቢ ያደረገ ሲሆን፤ ይህም ህብረተሰቡ የመሬት አስተዳደር፣ የኢንቨስትመንት፣ የገቢዎችና ሌሎችንም የመንግሥት አገልግሎቶች በኦንላይንና በአካል ማግኘት የሚያስችል ነው።
አገልግሎቱ በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳር እና በሌሎችም የክልሎች ከተሞች ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን፤ ማዕከላቱን በየደረጃው እስከ ወረዳ ድረስ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተንቀሳቃሽ መሶብ አገልግሎትን በአዲስ አበባ ባስጀመሩበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት የቆዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎችን በመፍታት የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተውታል።
ይህንን ለማሳካት በመንግሥት፣ በግል ኩባንያዎችና በእያንዳንዱ ዜጋ ዘንድ የባህልና የአስተሳሰብ ለውጥ መምጣት እንዳለበትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
ሀገሪቷን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መንግሥት በትኩረት እየሰራባቸው ካሉ አምስት የኢኮኖሚ አምዶዎች መካከል ቴክኖሎጂ አንደኛው መሆኑን ነው በወቅቱ ያብራሩት።
ቴክኖሎጂ የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የቱሪዝም ዘርፍን ለማዘመን እንዲሁም ዲጂታል የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት ሁሉንም የልማት ዘርፎች የሚያቀናጅ ዋና መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡበት ሲሆን፤ በተለይም የአገልግሎት አሰጣጥን ወደ ዘመናዊና ዲጂታል ሥርዓት በመቀየር የዜጎችን እንግልት መቀነስ አስችሏል።
የ“ዲጂታል 2030” ስትራቴጂ፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችን ይበልጥ በማጠናከር ሀገራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግርም አብራርተዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አለማየሁ በበኩላቸው እንደተናገሩት፤ በሀገሪቷ ባሉ ከ108 በላይ ማዕከላት ከ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት ተችሏል።
የአገልግሎቱ አጠቃላይ ሀገር አቀፍ የተገልጋዮች እርካታ መጠን ከ99 በመቶ በላይ መሆኑን ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
በዘመናዊ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት መስጫዎች ማዕከላት በአካል መጥተው መገልገል ለማይችሉ ዜጎች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንና ተደራሽነትን ይበልጥ ለማስፋት እየተሰራ መሆኑን አጽንኦት መስጠታቸው ይታወሳል።
በመዲናዋ የተዘረጋው የዲጂታል መሶብ አገልግሎት፣ በከተማ ደረጃ እየተካሄደ ላለው የዲጂታል ሽግግር ማሳያ ከመሆኑም በላይ በነዋሪዎች ዘንድ ትልቅ ተስፋን ጥሏል።