የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ትኩረት ሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ትኩረት ሰጥቷል
አዳማ፤ጳጉሜን1/2018(ኢዜአ)-መጪውን የዘመን መለወጫ በዓል ምክንያት በማድረግ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ አስታወቀ።
በአዳማ ከተማ ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል የተዘጋጀ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቷል።
የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ ሃላፊ የሺ ጂማ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፣ በክልሉ የዘመን መለወጫ በዓልን ተከትሎ በፍጆታ ምርቶች ላይ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኝ ኤግዚቢሽንና ባዛር ተከፍቷል።
ባዛሩ ለአምራቾች የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ ሸማቾች የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲሸምቱ የሚያስችላቸውና የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚያግዝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአዳማ ከተማ ህገ ወጥ ንግድን በመከላከልና ምርቶች ቀጥታ ለሸማቹ እንዲቀርብ በማድረግ በኩል ያለውን ተሞክሮ ወደ ሌሎች የክልሉ ዞኖች ለማስፋፋት እንሰራለን ብለዋል።
የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሃይሉ ጀልዴ በበኩላቸው እንደገለጹት ከተማ እሰተዳደሩ የሌማት ትሩፋት መርሀግብርን ተግባራዊ በማድረግ አምራቹን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ ገበያን ለማረጋጋት ትኩረት ሰጥቶ አየሰራ ነው።
በዚህም የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግም በምግብ ራስን ለመቻልና የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ መቻሉን ጠቁመዋል።
የእመርታን ቀን ምክንያት በማድረግ የክልሉ መንግስት አመራሮችና የመስተዳድሩ የሥራ ሃላፊዎች የልማት ሥራዎች ጎብኝተዋል።