የ"ጎቤ እና ሽኖዬ" ባህላዊ ጨዋታዎች ለቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው - ኢዜአ አማርኛ
የ"ጎቤ እና ሽኖዬ" ባህላዊ ጨዋታዎች ለቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አላቸው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የ"ጎቤ እና ሽኖዬ" ባህላዊ ጨዋታዎች የሕዝቦችን አብሮነትና ማኅበራዊ ትስስር ከማጠናከር ባለፈ ቱሪዝምን በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።
የ'ጎቤና ሽኖዬ' ባህላዊ ጨዋታዎች የክረምት ወቅት አልፎ የበጋ ወቅትን በደስታና በፍቅር ለመቀበል ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው በአንድነትና በነጻነት ደስታቸውን የሚገልጹበት ነው።
በባህል አልባሳት የተዋቡትና የደመቁት ወጣቶችና ልጃገረዶች በባህላዊ ጨዋታው የተፈጥሮን መታደስ የሚያበስሩበት እና የእርስ በርስ ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበትም ነው።
ጭጋጋማው ክረምት አልፎ ብሩሁ የፀደይ ወቅት ሲተካ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች፣ ወንዶችና ልጃገረዶች የ"ጎቤ እና ሽኖዬ" ባህላዊ ጨዋታዎችን ይጫወታሉ።
ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶችም በዛሬው ዕለት የ"ጎቤ እና ሽኖዬ" ባህላዊ ጨዋታዎችን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ተዘዋውረው አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ጀሚላ ሲምቢሩ በፌስቲቫሉ ላይ እንደገለጹት፤ የክልሉ መንግሥት የኦሮሞን የቀደመ ባህል፣ እሴት፣ ማንነትና ታሪክ ወደ ነበረበት ለመመለስ ውጤታማ ሥራዎችን አከናውኗል።
ቢሮው የኦሮሞን ሕዝብ ባህልና እሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅና የቱሪስት መስህብ በማድረግ ለሀገር ኢኮኖሚ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲኖራቸው ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑንም ገልጸዋል።
ከኦሮሞ ባህላዊ እሴቶች መካከል አንዱ የጎቤና ሽኖዬ ባህላዊ ጨዋታዎች እንደሚጠቀስ ገልጸው፤ ባህላዊ ጨዋታዎቹ የክረምት ወቅት አልፎ የበጋ ወቅትን በደስታና በፍቅር ለመቀበል ወጣት ወንዶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው በአንድነትና በነጻነት የሚጫወቷቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ባህላዊ ክዋኔው የትውልዱን ሥነ ልቦና ለመቅረጽ ካለው ፋይዳ ባለፈ፣ የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ አበርክቶውን ለማጠናከር ያስችላል ብለዋል።
ወጣቶች የጎቤና ሽኖዬን ባህላዊ እሴት ጠብቀው ለማቆየትና ለሚቀጥለው ትውልድ ለማስተላለፍ እያደረጉት ያለውን ጥረት አድንቀው፣ በቀጣይም ወጣቶች ጨዋታውን ሲጫወቱ እሴቱን በጠበቀ መልኩ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የክልሉ ሕዝብ የዳበረ ባህሉንና እሴቱን መሠረት አድርጎ ሕይወቱን እንዲመራ ለማስቻል የባህል ፍርድ ቤት፣ የበጎ አድራጎት አገልግሎት እንዲሁም የጋቻ ሲርና እና ቡሳ ጎኖፋ ሥርዓቶች ተቋማዊና ስልታዊ በሆነ መንገድ እየተተገበሩ መሆናቸውንም አያይዘው ገልጸዋል።