ቀጥታ፡

በሶማሌ ክልል የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እውን እያደረጉ ነው

ጅግጅጋ፣ጳጉሜን 1/2018(ኢዜአ)፦ በሶማሌ ክልል ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እውን እያደረጉ  መሆኑን የክልሉ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አህመድ ረሺድ ገለጹ።

በክልሉ ያለውን እምቅ ሃብትና ምቹ እድሎች በመጠቀም በሁሉም ዘርፎች የተቀናጀ የልማት ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተጨባጭ ውጤትና ቀጣይነት ያለው ስኬት እየተመዘገበ ህዝቡም ተጠቃሚ መሆን ችሏል።

በክልሉ ጳጉሜን 1 "የእምርታ ቀን" እነዚህን ስኬቶች በማስታወስ ለቀጣይ የልማት ስራዎች ይበልጥ ለመትጋት በሚያስችል ሁኔታ እለቱ በጅግጅጋ ከተማ ተከብሯል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ንግግር ያደረጉት የሶማሌ ክልል የኢንቨስትመንትና የኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አህመድ ረሺድ፤ ከልማት እርቆና ተረስቶ የቆየው የሶማሌ ክልል ያልተቋረጠ ልማት ላይ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት እውን እያደረጉ  መሆኑን ገልጸዋል።

በተጠናቀቀው በጀት አመት ብቻ 530 ባለሃብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ወደ ስራ መግባታቸውን ለአብነት አንስተው ከምርትም ባለፈ ለበርካታ ዜጎች ስራ መፍጠሩን ተናግረዋል።

የክልሉ የግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አብዱረህማን ኑር በበኩላቸው በመደበኛ የምርት ወቅቶችና በመስኖ ጭምር በማልማት የክልሉ የግብርና ምርታማነት እያንሰራራ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

በዚህም የምግብ ዋስትናንና የቤተሰብ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የራሱን ድርሻ ማበርከቱን አስረድተዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የክልሉ የሥራ ሃላፊዎች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም