ቀጥታ፡

በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦በእንስሳት ሀብት ልማት ዘርፍ ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ለውጥ መመዝገቡን የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስራት ጤራ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የእንስሳት ተዋፅዖ ምርታማነትን መጨመር ማስቻሉንም ተናግረዋል። 

ባለፉት ዓመታት በብዝሃ ኢኮኖሚ ዘርፍ ትኩረት ከተሰጣቸው መካከል በግብርናው ዘርፍ የእንስሳት ሃብትና ተዋፅዖ ምርትና ምርታማነት ላይ በተከናወኑ ተግባራት ውጤታ ማስመዝገብ ተችሏል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይፋ በተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብርም የወተት፣ ዶሮ፣ እንቁላልና ሥጋ፣ በዓሳና በንብ ማርባት ብሎም ማር ምርት ላይ ለውጥ ተመዝግቧል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አስራት (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ከእንስሳት ሀብት የሚፈለገውን ጥቅም ለማግኘት ባለፉት ዓመታት ዘርፈ ብዙ ተግባራት ሲከናወን በመቆየቱ እመርታዊ ለውጥ ተመዝግቧል፡፡

በተለይም በሥጋ ወጪ ንግድ እንዲሁም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከፍተኛ ስኬት እና ምርታማነት መመዝገቡን ገልጸዋል፡፡

በተለይም የተቀናበሩና ጥራታቸው የተጠበቀ ሥጋና የሥጋ ውጤቶችን ወደ ውጭ በመላክ በኩል ከታቀደው በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ ይህም የዘርፉን አቅም ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገረ አዎንታዊ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በወተት፣ በዶሮ እንቁላልና ሥጋ፣ በአሳ እንዲሁም በንብ ማር ምርታማነት ላይ ጉልህ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

ይህ ስኬት የሴቶችና የወጣቶችን የሥራ ዕድል ከማስፋት ባለፈ፣ በቤተሰብ ደረጃ የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

በሌማት ትሩፋት፣ በወጪ ንግድ እና በተለይም በእንስሳት ዘርፍ የተመዘገቡት ድሎችና አዎንታዊ ውጤቶች ለቀጣይ ሥራዎች እንደ መስፈንጠሪያ ሆነው እንደሚያገለግሉ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተገኙት ስኬቶች የዘርፉን እመርታ ያሳደጉ መሆናቸውን አመልክተው፤ በቀጣይ ሂደት በከፍተኛ ቁርጠኝነትና በላቀ ሞራል ለመስራት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አስረድተዋል።

ዘንድሮ የተመዘገበውን የምርታማነት መነሻ በማድረግና የተገኙትን ድሎች በማሳደግ የላቀ የምርት ውጤት ለማስመዝገብ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም