በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ይጠናከራሉ
ሆሳዕና፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ግብርናን በማስፋፋት የተመዘገቡ እመርታዊ ለውጦች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የጳጉሜን 1 "የእመርታ ቀን"ን በማስመልከት "እመርታ ለዘላቂ ልማት" በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የግብርና ልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ በከምባታ ዞን ተካሂዷል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፡፡
በክልሉ ባለፉት ሦስት ዓመታት ዘመናዊ ግብርናን ለማስፋፋት በተሠሩ ሥራዎች ተጨባጭ እመርታዊ ለውጦችን ለማስመዝገብ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በክልሉ የማሳ ሽፋን በ2016 በጀት ዓመት 980 ሺህ ሄክታር መሬት እንደነበር አቶ ኡስማን አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ለማድረስ ተችሏል ብለዋል።
ዓመታዊ የምርታማነት መጠን 106 ሚሊዮን ኩንታል ከነበረበት ወደ 161 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ማሳደግ እንደተቻለም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ኡስማን ገለጻ የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ትግበራው የእንስሳት፣ የማር፣ የዶሮና የእንቁላል ምርታማነት እንዲጨምር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል የወተት ምርታማነትን ማሳደግ በመቻሉ የአርሶ አደር የወተት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩም ተናግረዋል።
የዘመኑ አርበኝነት ከድህነት መውጫ መንገዶችን አሟጦ በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሆነ ያነሱት ኃላፊው፣ በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል ብለዋል።
የከምባታ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ ሄራም በበኩላቸው እንዳሉት፣ በዞኑ ባለፉት ዓመታት በግብርና መስክ ያሉ ዕድሎችን አሟጦ ለመጠቀም በተሠሩ ሥራዎች ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር መተግበሩ በዞኑ ከ850 በላይ የወተት፣የዶሮ፣ የንብና የማር መንደሮች መደራጀታቸውን ጠቁመዋል።
የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ሰብሎችን በስፋት ከማልማት በተጨማሪ የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፉ ቡናና የቅመማ ቅመም ምርቶች እንዲመረቱ አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውንም አስረድተዋል።
በዘርፉ እየተመዘገቡ ያሉ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን የማረጋገጥ ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ገልጸዋል።
በዱራሜ ከተማ በጥምር ግብርና የተሰማሩት ወይዘሮ ተዋበች ታደሰ አራት ሄክታር ማሳቸውን በጥምር ግብርና በማልማት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ለኤክስፖርት የሚሆን ቡና እና ማር እያመረቱ እንደሚገኙ ገልጸው፣ በዘርፉ እየተደረገላቸው ባለው ድጋፍ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የከምባታ ዞንና የዱራሜ ከተማ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።