በደብረ ብርሃን ከተማ 29 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በደብረ ብርሃን ከተማ 29 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተዋል
ደብረ ብርሃን ፤ጳጉሜን 1/2018(ኢዜአ)፡- በደብረ ብርሃን ከተማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 29 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች መሰማራታቸውን የከተማ አስተዳደሩ አንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ገለጸ።
የኢንዱስትሪ ዘርፉን ምርታማነት በማሳደግ ለዜጎች ተጠቃሚነትና የሀገር እድገት መሰረት እንዲሆን ባለፉት ጥቂት አመታት ከፖሊሲ ለውጥ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም ዘርፉ እመርታ እያስመዘገበ የበርካታ ዜጎች የስራ መስክና የውጭ ምንዛሬ ወጪን በመቀነስም የላቀ አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል።
በአማራ ክልል የደብረ በርሃን ከተማ የኢንዱስትሪ ማእከል ሆና በርካታ ኢንቨስተሮችን እያስተናገደች እድገትና ማንሰራራት እያሳየች ትገኛለች።
ከዚሁ ጋር በተገናኘ ኢዜአ ያነጋገራቸው የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ ብርሃን ገብረህይወት፣ በከተማዋ የኢንቨስትመንት ዘርፉ በርካታ ባለሃብቶችን በመሳብ ለውጥና እድገት በማሳየት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ 29 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ካፒታል ያስመዘገቡ ባለሃብቶች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፣ በግብርና በማዕድን እና በሌሎችም ዘርፎች የኢንቨስትመንት ፈቃድ በመውስድ ወደ ስራ መግባታቸውን አንስተው እስካሁን 22 ኢንዱስትሪዎች ወደ ምርት መግባታቸውን ገልጸዋል።
በጨርቃጨርቅ፣ በቆዳና ሌሎችን ጨምሮ በዓመቱ ለውጪ ገበያ ከቀረበው ምርታቸው 137 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የሚተካ 70 ሺህ 636 ቶን ተኪ ምርት በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ የታቸለበትን ስኬትም አንስተዋል።
በዚህም 589 ሚሊየን ዶላር የውጪ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን የገለጹት ሃላፊው የዘርፉን እመርታ የሚያሳዩ በርካታ ውጤታማ መገለጫዎች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከተሰመሩ ባለሃብቶች መካከል በላይነህ ቢዝነስ ግሩብ የፊቤላ ደብረብርሃን መኪና መገጣጠሚያ ስራ አስኪያጂ አቶ መሐመድ አህመድ፤ በዘርፉ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታና የመንግስት ድጋፍ ታክሎበት ዘርፉ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል እየተፈጠረበት፣ የእውቀት ሽግግርና የውጭ ምንዛሬ እየተገኘበት እንዲሁም የሀገር ውስጥ የምርት ፍላጎት እየተስተናገደበት ይገኛል ብለዋል።