ኢትዮጵያ እመርታዊ ውጤቶችን እያስመዘገበች ወደ ላቀ ብልፅግና እየተጓዘች ትገኛለች-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እመርታዊ ውጤቶችን እያስመዘገበች ወደ ላቀ ብልፅግና እየተጓዘች ትገኛለች-ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ እያመረተች በርካታ እመርታዊ ውጤቶችን እያስመዘገበች ወደ ላቀ ብልፅግና እየተጓዘች ትገኛለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች የጀመረችውን ሁለንተናዊ የለውጥና የብልፅግና ጉዞ በማጠናከር ከተረጅነት ወደ አምራችነት በጽኑ መሸጋገር ላይ እንደምትገኝም ተናግረዋል።
ዛሬ ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም "እመርታ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት" በሚል መሪ ቃል "የእመርታ ቀን" በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የአጋር ድርጅቶች እና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች ተገኝተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ወቅት፤ ባለፉት ዓመታት የተተገበሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና የፋይናንስ ሥርዓት ማዘመኛ እርምጃዎች የኢኮኖሚውን መሠረት ማጠናከራቸውን ገልጸዋል።
በተለይም የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት እመርታዊ ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም በሥጋ፣ በሩዝ፣ በበቆሎ፣ በወተት እና በሌሎችም ሰብሎች በሌማት ትሩፋትና በክላስተር እርሻ አማካኝነት የተመዘገቡት ስኬቶች የኢትዮጵያን ምግብ የማምረት አቅም ማሳደጋቸውን ገልጸዋል።
በማኑፋክቸሪንግና አግሮ ኢንዱስትሪ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄና በኢንዱስትሪ ፓርኮች አማካኝነት የውጭ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት በመተካት ኢትዮጵያን ከሸማችነት ወደ አምራችነትና ተወዳዳሪነት መዋቅራዊ ሽግግር ማድረጓን ተናግረዋል።
በማዕድን ዘርፍ የተፈጥሮ ሀብትን በእሴት ጭማሪ ወደ ከፍተኛ ኢኮኖሚ በመለወጥ አዳዲስ የኤክስፖርት ዕድሎች መፈጠራቸውን አብራርተዋል።
በገቢዎችና ጉምሩክ ዘርፍ የኢ-ፋይሊንግ፣ የኢ-ፔይመንት እና የአሠራር ዲጂታላይዜሽን ግልጽነትና ቅልጥፍናን በማምጣት የታክስ ሕግ ተገዥነትን ማጠናከራቸውን ጠቁመዋል።
አምራችነት እሳቤ፣ ስልት እና ግብ መሆን እንዳለበት ያሰመሩበት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማናቸውም ሥራ እና ፕሮጀክት እሴት ካልጨመረና ምርት ካላተረፈረፈ ብክነት እንደሆነ ገልጸዋል።
የአገልግሎት አሰጣጥን ከእጅ መንሻና ከሙስና ነጻ ለማድረግ አሠራሮችን ወደ ዲጂታል ማሸጋገር እንደሚገባም አሳስበዋል።
ኢትዮጵያ እየተለወጠች፣ እያንሰራራች፣ እያመረተች ወደ ላቀ ብልጽግና እየተጓዘች እንዳለች ተናግረው፤ ለዚህ የኢትዮጵያ ከፍታ በተሰማሩበት ዘርፍ ሌሊትና ቀን ለደከሙ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ወዳጆች እና አጋሮች ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።