የአፋር ክልልን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልልን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ ነው
ሰመራ፣ጳጉሜን 1/2018(ኢዜአ) ፡-የአፋር ክልልን እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ ኡመር ኑር ገለጹ።
"የእመርታ ቀን" በአፋር ክልል ሰመራ ከተማ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የመሬት ቢሮ ኀላፊ ኡመር ኑር ፤ የአፋር ክልል ብዙም ሳይለማ የቆየ ሰፊ መሬትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በተለይም በመስኖ ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት መኖሩን በማንሳት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የበጋ መስኖን ጨምሮ ሌሎችም የግብርና ልማት ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።
የመሰኖ ስራዎችን በማጠናከር መሬት በተጠናከረ አቅም ወደ ምርት ለማስገባት በሚደረገው ጥረት በርካታ ወጣቶች እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸው ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት በተሳካ ሁኔታ መቀጠሉን ተናግረዋል።
የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ አኗኗር መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎች በመጠናከር ተጠቃሚ ማድረግ በመቻሉ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት ጥሩ መሰረት እየያዘ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፋር ክልልን ሰፊ መሬትና እምቅ የተፈጥሮ ሃብት በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።
የአፋር ክልል የፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ኀላፊ አብዱ መሐመድ፤ ባለፉት ስምንት ዓመታት አፋር ክልልን የተለየ ገፅታ ያላበሱ ስኬታማ የልማት ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
በተለይም በግብርና ፣ኢንዱስትሪ በማዕድንና አንሰሳት ልማት እመርታዊ ስኬት ስለመመዝገቡ ተናግረዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት በየደረጃው ያሉ የክልሉ አመራሮችና የሠመራ ሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች የችግኝ ተከላ አካሂደዋል።