ቀጥታ፡

በአማራ ክልል የሚከበሩ ህዝባዊና ኃይማኖታዊ በዓላት የቱሪስት ፍሰቱን ጨምረዋል

ባህር ዳር፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ) ፦ በአማራ ክልል በአደባባይ የሚከበሩ ህዝባዊና ሀይማኖታዊ በዓላት የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደጉ መምጣታቸውን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ ገለጹ።

የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ ቡሄና እንግጫ ነቀላ በዓላት የመዝጊያ መረሃ-ግብር "ባህላዊ እሴቶቻችን የፈተና መሻገሪያ የጋራ ተስፋችን መገንቢያ" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ ተከናውኗል።


 

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በመርሃ ግብሩ ላይ እንደገለጹት የአማራ ክልል የበርካታ የተፈጥሮ፣ የሰው ሰራሽ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ባለቤት ነው።

ከዚህ መካከል ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል፣ እንግጫ ነቀላ፣ ቡሄና ሌሎች በአደባባይ የሚከበሩ በዓላት የቱሪስት ፍሰቱን ዓመቱን ሙሉ በማድረግ ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዓላቱን ለቱሪስት መስህብነት በማዋል የኢኮኖሚ ጠቀሜታቸውን ከማሳደግ ባለፈ የሕብረ ብሔራዊነት መገለጫነታቸውን ለማጉላት ይበልጥ መስራት እንደሚገባ አስረድተዋል።


 

በቀጣይም የበዓላቱን እሴት ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ባለድርሻ አካላት ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለልና እንግጫ ነቀላ በዓላት የልጃገረዶች አንድነትና ነጻነት ደምቆ የሚታይበት ነው።

በዓላቱ የፍቅር፣ የመተሳሰብና የትብብር እሴቶች መገለጫ በመሆናቸው፣ ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን አስረድተዋል።


 

የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ መልካሙ ፀጋዬ በበኩላቸው በዓላቱ የተስፋ፣ የነጻነትና የትብብር ተምሳሌት መሆናቸውን አስታውሰው፣ የክልሉን እምቅ የቱሪዝም ሀብት አጉልቶ ለማሳየት ያስችላሉ ብለዋል።

ባህላዊ እሴቶቹን ለማህበረሰባዊ ትስስር ለማዋል ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

በድምቀት በተከበረው የቡሄ፣ ሻደይ፣ አሸንድዬ፣ ሶለል እና እንግጫ ነቀላ የመዝጊያ ሥነ ስርአት ላይ የክልሉ አመራሮችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም