ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው ብዝሃ መር የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው ብዝሃ መር የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ነው
ዲላ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ) ፦ኢትዮጵያ እየተከተለችው ያለው ብዝሃ መር የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።
ቀደም ሲል በግብርና መር ኢኮኖሚ ልማት ላይ ተወስና የቆየችው ኢትዮጵያ በመደመር መንግሥት ወደ ብዝሃመር የኢኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ተሸጋግራለች።
የኢትዮጵያን እምቅ የመልማት አቅሞች በመገንዘብ የግብርና ልማትን ጨምሮ በኢንዱስትሪ፣ ቱሪዝም፣ አይሲቲና የማዕድን ዘርፍ ዋነኛ የልማት ምሰሶዎች ሆነው እየተሰራባቸው ይገኛሉ።
በእነዚህ ዘርፎችም ላይ በተሰሩ ስራዎች ሀገሪቱ እመርታዊ እድገትና ማንሰራራት ላይ ለመሆኗ በርካታ ተጨባጭ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንትና የተፈጥሮ ሃብት ተመራማሪ ሐብታሙ ተመስገን (ዶ/ር)፤ የልማት ስትራቴጂው ብዝሃ መሆኑ እና ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም መደረጉ ለተመዘገበው ስኬት የላቀ ትርጉም አለው ብለዋል።
የብዝሃ ኢኮኖሚ እድገት አማራጭን ከመከተል ባለፈ በተለይም በግብርናው ዘርፍ አዳዲስ ኢንሼቲቮችን በመተግበርና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ትልቅ እመርታ መታየቱን አስረድተዋል።
በስንዴ ልማት፣ በቡና ልማት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ሌሎች የግብርና ዘርፎች ውጤቱና ስኬቱ አስደናቂ መሆኑን ነው ያነሱት።
የተፈጥሮ ሃብትና መሬት አስተዳደር ተመራማሪና የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው እንዳሉት ፤ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችን በመጠቀም እየተሄደበት ያለው የልማት ዕቅድ በአጭር ጊዜ ውጤት አምጥቷል።
በተለይም በግብርናው ዘርፍ የተጀመረው የተቀናጀ የልማት ጥረት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነትና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ መሰረት መሆኑን አንስተዋል።
ከመደበኛ የምርት ወቅት በተጨማሪ የመስኖ ልማት ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸው፣ የዘርፉ እመርታ በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም ያላቸውን እምነት ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ የታየው እመርታ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመውጣትና ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባት መሰረት የሚጥል መሆኑን ምሁራኑ ገልጸዋል።