ቀጥታ፡

የመንግሥት አዳዲስ እሳቤዎች በተለያዩ መስኮች የሚጨበጡ እመርታዎች እንዲመዘገቡ አድርገዋል - የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች

አዳማ ፤ ጳጉሜን 01/2018 (ኢዜአ) ፦ ያለፉት ዓመታት በመንግሥት አዳዲስ እሳቤዎችና በህዝቡ ትብብር በተለያዩ መስኮች የሚታዩና የሚጨበጡ እመርታዎች መመዝገባቸውን የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ገለጹ።

የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ወደ አዲስ ዓመት በሚደረገው ሽግግር የጳጉሜን 1 'የእመርታ ቀን' አስመልክተው ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ፓርቲ ምክትል ሰብሳቢ አቶ በየነ ደሳለኝ፤ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች መከበራቸው ሀገሪቱ ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች በማንሳት ቀጣይ ስንቅ ለማድረግ የሚያነሳሳ ይሆናል ብለዋል።

መንግሥት ባለፉት ዓመታት በሀገር በቀል እሳቤዎችና ፖሊሲዎች ሀገራዊ አቅሞችን መጠቀም ያስቻሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና በርካታ የልማት ኢንሼቲቮችን በመተግበር አስደናቂ እመርታዎች ማስመዝገቡን አንስተዋል።

በተለይም በግብርናው ዘርፍ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ላይ የመጣው ለውጥ እና የታየው ስኬት ሊደነቅ የሚገባው ነው ብለዋል።

የተለያዩ የግብርና ኢንሼቲቮች የተረጂነትና የጠባቂነት አስተሳሰብን በማስወገድ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የዜጎችን ተጠቃሚነት ያረጋገጡ መሆኑንም አንስተዋል።

በሌሎችም ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችም እመርታ የተመዘገበባቸውና አመርቂ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በድምሩ ባለፉት ዓመታት በመንግሥት አዳዲስ እሳቤዎችና በህዝቡ ትብብር በተለያዩ መስኮች የሚታዩና የሚጨበጡ እመርታዎች የተመዘገቡበት መሆኑን ተናግረዋል።

የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ሥራ አስፈጻሚ እና የኦሮሚያ ክልል አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ተሰማ፤ በመንግሥት ሀገር በቀልና አዳዲስ እሳቤዎች በመታገዝ ባለፉት ጥቂት አመታት አስደናቂ ውጤት መመዝገቡን ተመልክተናል ብለዋል።

የውጭ ምንዛሪ እጥረትንና የዋጋ ግሽበትን በመቋቋም ጭምር የሀገሪቱን ገጽታ የቀየሩ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በጥራት እና በፍጥነት በመፈጸም የላቀ እመርታ መታየቱንም አንስተዋል።

በጥናት ላይ ተመስርቶ በሀገሪቱ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ መደረጉ ለዜጎች ሰፊ የስራ እድልን ከመፍጠር ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ወጪን በመቀነስ ረገድ ትርጉም ያለው ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የምሥራቅ ሸዋ ዞን አስተባባሪ ወይዘሮ ሠናይት በላይ፤ በአዲሱ ዓመት መባቻ ላይ የጳጉሜን ቀናት በተለያዩ ስያሜዎች መከበራቸው በጎ ሀሳቦችን እንድናፈልቅ ልዩ ስሜት እንዲፈጠርብን ያደርጋል ብለዋል።

መንግሥት በጥቂት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት በማሸጋገር በተለይም በመስኖ ስንዴን በማልማት ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መቻሉ ትልቅ እመርታ መሆኑን ገልጸዋል።

በቱሪዝም፣ ዲጂታላይዜሽን፣ የአረንጓዴ አሻራ ልማት፣ በአትክልትና ፍሬፍሬ ልማት እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች እመርታ መመዝገቡን ማየት ችለናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም