ቀጥታ፡

ሀገራዊ እመርታዎች ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት ጥለዋል-ምሁራን

ሮቤ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡ ሀገራዊ እመርታዎች ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት መጣላቸውን የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ገለጹ።

ዛሬ ጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም "የእመርታ ቀን" በሚል መሪ ሐሳብ በሀገር አቀፍ ደረጃ በደማቅ ሁኔታ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ይገኛል።

መርሐ ግብሩ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪና በዲጂታል ዘርፎች ያስመዘገበቻቸውን ሁለገብ ስኬቶችና መዋቅራዊ ለውጦች ከማሳየት ባሻገር ልማቱን ለማስቀጠል ያለመ ነው።

የመደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ሀገራዊ ዕድገትን ለማሳካት የተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና መዋቅራዊ ለውጦች ዘላቂ ልማትን ለማስመዝገብ መሠረት እየጣሉ መሆናቸውን አንስተዋል።

በዩኒቨርሲቲው የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ኮሌጅ ዲንና ተመራማሪ ደረጄ ደርሶ (ዶ/ር) እንዳሉት የግብርናውን ዘርፍ በማሳደግ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ገበያን በማረጋጋት በኩል ተጨባጭ ውጤት መጥቷል።

በተለይም ቀደም ሲል ዝናብን ብቻ በመጠበቅ የሚከናወን እርሻን የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ወደ መስኖ ልማት በመግባት ዓመቱን ሙሉ ማልማት ማስቻሉ አንድ እመርታ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌላው በዩኒቨርሲቲው የግብርና ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ተስፋዬ አመኑ በበኩላቸው፣ በቆላማ አካባቢዎች የተከናወኑ የግብርና ሥራዎች የአርብቶ አደሩና የአርሶ አደሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚነት ማሳደጋቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን የእንስሳት ጤና እና የእርባታ ዘዴን በማሻሻል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ማሳደጋቸውን ጠቅሰዋል።

ረዳት ፕሮፌሰሩ እንዳሉት መንግሥት ያመቻቸው ምቹ የሥራ አካባቢና የገበያ ትስስር ለዚህ ስኬትና እመርታዊ ሽግግር አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።

ባለፉት ዓመታት በግብርና፣ በቱሪዝም፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ብዝኃ የኢኮኖሚ ዘርፎች የታዩት እመርታዊ ለውጦች የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መሠረት ያጠናከሩ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላው የዩኒቨርሲቲው የኢኮኖሚክስ መምህር ብርሃኑ ጌታቸው ናቸው።

በተለይ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሙ እና ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ለብዝኃ ዘርፎች ዕድገት ከፍተኛ ድርሻ ማበርከታቸውን አመልክተዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ አምራቾችን አቅም በማጎልበት የምርት መጠንና ጥራት እንዲጨምሩ ማድረጉን ጠቁመው፤ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ ውጤታማ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም