የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ስኬቶችን በማላቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል- ከንቲባ ከድር ጁሃር - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ስኬቶችን በማላቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ትኩረት ተሰጥቷል- ከንቲባ ከድር ጁሃር
ድሬዳዋ፣ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፡- የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ስኬቶችን በማላቅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአየር ንብረት ለውጥ ሚዛንን ለመጠበቅ ትኩረት መሰጠቱን የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።
የእምርታ ቀን በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ በመትከልና እና በሌሎች ዝግጅቶች በድሬዳዋ እየተከበረ ነው።
"እምርታ ለኢትዮጵያ ከፍታ" በሚል መሪ ሃሳብ በክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፓርክ የችግኝ ተከላ መርሀግብር ተካሂዷል።
ከንቲባ ከድር ጁሃር በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን በማላቅ ለምግብ ዋስትና መረጋገጥና የአየር ሚዛን ለመጠበቅ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።
የመደመር መንግስት ባለፉት ዓመታት ተግባራዊ ካደረጋቸው እና የአገር የከፍታ ጉዞ ዕውን ከሆኑባቸው ተግባራት መካከል አንዱ የአረንጓዴ አሻራ መሆኑን አንስተዋል።
በድሬዳዋ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብሮች ችግኞች የአካባቢውን ስነምህዳር በመለወጥ፣ የከርሰ ምድር ውሃ እንዲጨምር በማገዝና የተመናመነውን ደን በመመለስ ወሳኝ ሚና ማበርከታቸውን አስታውቀዋል።
በተለይ በድሬዳዋ ሲከሰት የነበረን የጎርፍ አደጋን በላቀ ደረጃ በመቀነስና ውሃን ወደ ጥቅም ለመለወጥ እያበረከተ ያለው አስተዋፅኦ ለማስቀጠል ችግኞች በላቀ ህዝባዊ ተሳትፎ እየተተከሉ ይገኛሉ ብለዋል።
ዛሬም በእምርታ ቀን በህዝብ እና በአመራሩ ተሳትፎ የተተከሉት ችግኞች የተገኘውን እመርታ ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው አንስተዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኑረዲን አብደላ በበኩላቸው እንዳሉት፣ የእምርታ ቀን በአረንጓዴ አሻራ መርሀግብር የተገኙ ውጤቶችን በላቀ ደረጃ ለማስቀጠል መደላድል የተፈጠረበት ነው።
በተለይ መርሀግብሩ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውሀ ሀብት እንዲያድግ መሰረት በመጣሉ የገጠሩ ህብረተሰብ አነስተኛ መስኖ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለመሸጋገር እያገዘ ይገኛል ብለዋል።
የእምርታ ቀንን ምክንያት በማድረግ ዛሬ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሀግብር ላይ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳታፊ ሆነዋል።