በኢትዮጵያ የተመረተ፤ የመደመር መንግሥት እመርታዊ የኢንዱስትሪ ምርታማነት ፍኖት - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የተመረተ፤ የመደመር መንግሥት እመርታዊ የኢንዱስትሪ ምርታማነት ፍኖት
የመደመር መንግሥት የብዝኅ ኢኮኖሚ ልማት ፍኖተ ካርታ ኢትዮጵያን በሁለንተናዊ እመርታዊ የለውጥ ምኅዋር የምትጓዝበትን ዕድል ፈጥሯል።
ይህም በግብርና መር ክፍለ ኢኮኖሚ ብቻ ታጥሮ የቆየውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በማፍታታት የግብርና፣ ኢንዱስትሪ፣ ማዕድን፣ ቱሪዝምና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፎች ዕድገትን የሚያፋጥን ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።
በሁለት ምዕራፍ ተከፋፍሎ ተግባራዊ የተደረገው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብርም መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ስብራትን በማከም ንግድና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ አስቻይ ምኅዳር ፈጥሯል።
ይህም የዘርፎችን እመርታ በማላቅ የኢትዮጵያን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ መሰረት አስቀምጧል።
የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያም የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን በመፍታት በተኪና ወጪ ንግድ የኢንዱስትሪ ምርት የንግድ ተወዳዳሪነት ምርታማነትን የሚያልቅ እመርታዊ ውጤት አስገኝቷል።
በተለይም በማኑፋክቸሪንግና በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሰማሩ የሀገር ውስጥና ዓለም አቀፍ አልሚዎችን የኢንቨስትመንት ፍሰት በእጅጉ በማላቅ የኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ሽግግር እያፋጠነ ነው።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም በኢትዮጵያ የተመረተ በሚል የኢንዱስትሪ ምርት መለያ የሀገርን ዓለም አቀፍ ብራንድ በማጉላት የንግድ ሚዛንን የሚያስጠብቅ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአራተኛው ''የኢትዮጵያ ታምርት” ኤክስፖ መክፈቻ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ሀገራዊ ምርትን ማሳደግ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው ብለዋል።
ምርት አለማምረት ሀገርን ለጥገኝነት በመዳረግ ነጻነትን የሚያሳጣ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሁሉም ዘርፍ አምርቶ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በያዝነው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የ 10 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅና ይህ እድገት በዋናነት በኢንዱስትሪውና በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የመጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረውን የ3 ቢሊዮን ዶላር አፈጻጸም በሶስት እጥፍ በማሳደግ በያዝነው ዓመት 10 ቢሊዮን ዶላር ለማስገኘት መታቀዱን ገልፀው ንቅናቄው ሲጀመር 4 ነጥብ 7 በመቶ የነበረው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እድገት አሁን ላይ 10 ነጥብ 7 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል።
ባለፉት አራት ዓመታት በሀገር ውስጥ ምርት 14 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የገቢ ምርቶችን መተካት እንደተቻለና 993 ቆመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች እንደገና ወደ ስራ መመለሳቸውን ጠቁመው 3 ሺህ 680 አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ መግባታቸውን አክለዋል።
የፋይናንስ ዘርፍ ማሻሻያ እና አዲስ ህግ በአምራች ኢንዱስትሪው በኩል የመሬት፣ የኢነርጂ እና የፋይናንስ ተቋማት ችግሮች በሂደት እየተቀረፉ መሆናቸውን ገልጸው፤ አምራቾች የኢኮኖሚ አርበኝነት ስሜት ሊላበሱ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል እንደሚሉት የሀገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መዋቅራዊ ችግሮች በመፍታት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች እና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በኢኮኖሚው ላይ አወንታዊ ለውጥ እያመጡ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል በኢንዱስትሪው ዘርፍ ላይ ማነቆ የነበሩ መዋቅራዊ ችግሮችን በመፍታት በኩል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል።
ሪፎርሙ በባህሪው ሀገርን የውጭ ሸቀጥ ማራገፊያ የሚያደርጉ ቀደም ሲል የነበሩ የገበያ ተግዳሮቶችን በመፍታት በምንዛሬ ልዩነት ምክንያት የአምራቾች ጥቅም ይጎዳ የነበረውን አሰራር በመቀየር አምራቾች ምርታቸውን ወደ ውጭ በመላክ እንዲበረታቱ አድርጓል ነው ያሉት።
ያልተመጣጠነ የውጭ ምንዛሬን በመጠቀም ከውጭ ምርት አምጥቶ የመሸጥ አሰራርን በማስቀረት የሀገር ውስጥ አምራቾች ገቢ ምርቶችን እንዲተኩ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉን ለዘመናት የቆዩ የፖሊሲ፣ የሰው ኃይል፣ የግብአት እና የተቋማት ቅንጅት ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል።
በዚህም ቀደም ሲል ከ46 በመቶ እስከ 48 በመቶ ዝቅ ብሎ የነበረው የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አጠቃቀም፣ በተከናወነ የተቀናጀ ድጋፍ ወደ 66 ነጥብ 3 በመቶ ከፍ ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
ይህም አዳዲስ ፋብሪካዎችን ሳይገነቡ ባለው አቅም በመጠቀም በጥራትና በዋጋ ተወዳዳሪ ለመሆን አስችሏል ነው ያሉት።
ወደ 96 የሚደርሱ ስትራቴጂካዊ ምርቶችን በመለየት በተሰራው ስራ ከ1 ነጥብ 34 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ማዳን መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም የንግድ ሚዛን ክፍተቱን ከነበረበት 12 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር ወደ 9 ቢሊዮን ዶላር በመቀነስ የ25 በመቶ መሻሻል አሳይቷል ብለዋል።
የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው አመታዊ የእድገት መጠን በ2014 ዓ.ም ከነበረበት 4 ነጥብ 8 በመቶ በአሁኑ ወቅት ወደ 10 ነጥብ 7 በመቶ ያደገ ሲሆን በሀገሪቱ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ውስጥ ያለው ድርሻም ወደ 6 ነጥብ 9 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት።
አምራቾች በበኩላቸው መንግሥት ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና እያደረገ ያለው ዘርፈ-ብዙ ድጋፍ የፋብሪካዎችን የማምረት አቅም ማሳደጉን ይናገራሉ።
የቢጂአይ (BGI) ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሶሉሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማርታ ገላናው እንደገለጹት፤ ድርጅቱ ባሳለፋቸው ከ17 በላይ ዓመታት ውስጥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ድርጅታቸው የተለያዩ የእንስሳት መኖ ማቀነባበሪያ ማሽነሪዎችን በማምረት በሀገር ውስጥ እየተካ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በመንግሥት በኩል የሚደረገው ከፍተኛ ድጋፍና ማበረታቻ የማምረት አቅማቸው እንዲጨምር ማድረጉን ጠቅሰዋል።
ድርጅቱ በመንግሥት ሁለንተናዊ ድጋፍ ተወዳዳሪነቱ እያደገ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅት ከ200 ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ነው የሚናገሩት።
የሌጀንድ ኢንዱስትሪያል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሹሜ ሆርዶፋ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው ተኪ ምርትን በማምረት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የተለያዩ አልባሳትን፣ የተማሪዎች ዩኒፎርሞችን እንዲሁም የአውቶቡስ አሽከርካሪዎችና ረዳቶች ዩኒፎርሞችን እያመረተ ለገበያ እያቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።
በመንግሥት ቀጣይነት ያለው ድጋፍና ክትትል የመሠረተ-ልማት ችግሮች በመቀረፋቸው፣ ድርጅቱ የማምረት አቅሙን በማሳደግ ምርቶቹን በጥራትና በፍጥነት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም ጠቁመዋል።
በፋብሪካዎቹ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በበኩላቸው፤ በተፈጠረላቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሌጀንድ ኢንዱስትሪያል የሥራ ዕድል ያገኘው ዮናስ ግዛው ፤ የአምራች ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የሥራ ዕድል ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ ባለፈ የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ ረገድ ገንቢ ሚና እንዳለው ተናግሯል።
በቢጂአይ ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሶሉሽን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆነው ሓጎስ ካሳሁን በበኩሉ፤ አምራች ኢንዱስትሪዎች በመስፋፋታቸው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ መሆን መቻሉን ገልጾ፣ ይህም የሥራ ባህሉን ይበልጥ እንዲያዳብር እንዳስቻለው ተናግሯል።