ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የብዝኅ ዘርፍ እመርታ፡ የዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት መሠረት

ማኑፋክቸሪንግ፣ ከተማ ግብርና፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ ጨርቃ ጨርቅና ሌሎችም መስኮች ወጣቶች በስፋት ተሰማርተው ውጤታማ እየሆኑ የሚገኙበት የሥራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መስኮች ናቸው፡፡

ወጣቶቹ በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑ በመንግሥት በኩል ለወጣቶቹ እየተሰጠው ያለው የክህሎት ማበልጸጊያ ስልጠና፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ ማመቻቸትና በማኅበር ማደራጀት እስከ ብድር ማመቻቸት ድረስ እየተወሰደ ያለው ተግባር ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ይገኛል፡፡


 

በዚህም በርካታ ወጣቶች ተሰማርተው ውጤታማ ከመሆናቸውም ባለፈ ለሌሎችም የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም አስመልክተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ በተለያዩ ቦታዎች እየተካሄዱ ያሉ የገጠርና የከተማ ኮሪደር ልማቶች፣ ኢንዱስትሪ፣ ግብርና፣ ማዕድን፣ ሜጋ ፕሮጀክቶችና አዳዲስ የነፃ ንግድ ዞኖች መፈጠር ለሥራ ዕድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ዜጎች ውጭ ሀገርም ሄደው መስራት እንዲችሉ ከእንግሊዝ፣ ከጀርመን፣ ከፈረንሳይ፣ ከሳዑዲ ዓረቢያና ከሌሎች ሀገራት ጋር በተፈጠሩ ስምምነቶች የውጭ ሀገር የሥራ ዕድሎች ለሀገራችን ዜጎች መስፋፋታቸውን ተናግረዋል።

ሌላው አዲስ የሥራ መስክ የርቀት ሥራ (Remote Job) መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመው፣ በኢትዮጵያ ተቀምጠው ለውጭ ኩባንያዎች በቨርቹዋል መንገድ የሚሠሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።


 

የማዳበሪያ፣ የሪፋይነሪ፣ በክሪፕቶ ማይኒንግ የሚሠሩ ሥራዎችና የኤርፖርት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁና ሲስፋፉ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎች እንደሚፈጠሩም ጠቁመዋል።

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል እንደሚሉት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ለአዋጭ የሥራ ሀሳቦቻቸው የፋይናንስ ተደራሽነት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በተቋም ደረጃም የወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ኢንቨስትመንት ባንክ ለወጣቶች የሥራ ሀሳቦች የፋይናንስ ተደራሽነት ለማሳደግ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረዋል።

በየከተሞች እየተካሄዱ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችም የወጣቶችን ዕውቀት፣ ክህሎትና የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች መካከል አቤኔዘር እንግዳ እንደተናገረው፣ የከተማና ገጠሩን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል የዲጂታል ዕቁብ መተግበሪያ ማበልጸጉን ገልጿል፡፡

በዚህ መተግበሪያ አማካኝነት ክፍያዎችን መመዝገብና ያለው የዕቁብ ሂደት በተቀላጠፈ መንገድ እንዲካሄድ የሚያግዝ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዚህም ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ስታርትአፕ ችግርን በፈጠራ መንገድ መፍታት የሚያስችል አዲስ መስክና የሀገሪቱን የሥራ ዕድል ፈጠራ በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑን የገለጸው ደግሞ ወጣት በረከት ሺመክት ነው።

ስታርትአፖች፣ መንግሥትና ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶች በጋራ መሥራት እንዳለባቸው የጠቆመው ወጣት በረከት፣ ዘርፉ ለሀገር የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ገቢ ለማመንጨትም አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግሯል።

ሌላኛው ወጣት ሶፎኒያስ ዳዊት በበኩሉ፣ የአግሮ-ፕሮሰሲንግ ማሽነሪዎችንና የኮምፖስት ፕሮዳክሽን ላይን ማሽነሪዎችን በሀገር ውስጥ ዲዛይን በማድረግና በማምረት ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጿል።

ማሽነሪዎቹን በሀገር ውስጥ ማምረት የውጭ ምንዛሪ ወጪን እንደሚቀንስ ጠቅሶ፣ በሀገር ውስጥ በባህላዊ መንገድ የሚከናወኑ ሂደቶችንም በማደስ የመፍትሔ ማሽነሪዎችን እንደሚያቀርቡ ተናግሯል።

ወጣት ሶፎኒያስ ስታርትአፖች የሚሠሩባቸውን ዘርፎች በመለየት ትኩረት መደረጉ ለሚመጣው ትውልድ የሥራ ፈጠራ መንገድ እንዲታይ እንደሚያግዝ ገልጿል።

ይህም ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ ሲወጡ የሥራ ፈጠራ መንገድ እንዳለ እንዲያውቁና ስታርትአፕ ከሥራ ፈጠራና ለችግሮች መፍትሔ ከመስጠት አንጻር ትልቅ ድርሻ የሚጫወት ዘርፍ መሆኑን የሚያሳይ ነው ብሏል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም