ኢትዮጵያ በእመርታዊ ለውጦች ከዘመናት ድህነት በመላቀቅ ወደ ብልፅግና ጎዳና እየገሰገሰች ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በእመርታዊ ለውጦች ከዘመናት ድህነት በመላቀቅ ወደ ብልፅግና ጎዳና እየገሰገሰች ነው
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በእመርታዊ ለውጦች ከዘመናት ድህነት በመላቀቅ ወደ ብልፅግና ጎዳና እየገሰገሰች እንደምትገኝ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ እመርታ ለዘላቂ ከፍታ! በሚል ዛሬ እየተከበረ የሚገኘውን የእምርታ ቀንን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል።
እመርታ ከአሉበት የከፍታ ደረጃ ወደ ላይኛዉ መስፈንጠር ነው፤ ከፍታን በአዝጋሚ ሂደትም ዘመናትን ወስዶ ማሻሻል ይቻላል፤ በዚያ አግባብ የሚመጣ መሻሻል ከታለመዉ ግብ ለመድረስ የትውልዶችን ጥረት የሚጠይቅ መሆኑን ገልጿል።
ኢትዮጵያውያን ግን በቁጭት ለዘመናት ከቆየንበት ኋላ ቀርነት እና ድህነት በአዝጋሚ ጉዞ ለመላቀቅ ስለማይቻል እመርታዊ ለውጥ ማምጣትን ግብ አድርገን ሠርተን ስኬቶችን እያስመዘገብን ነው። ያለፉት ጥቂት ዓመታት ጥረቶቻችን ውጤቶች የሚያሳዩትም ይህንኑ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ጀርባ ያጎበጡ የውጭ ዕዳዎችን ጫና በመቀነስ፣ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅምን በማሳደግ፣ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት ዐቅም በማሻሻል፣ የማዕድን ሀብቶች አጠቃቀምን በማላቅ እመርታዊ ለውጦች መመዝገባቸውን አገልግሎቱ በመግለጫው አስታውቋል።
የመንግሥት አጠቃላይ የማድረግ ዐቅም በእጅጉ ተለውጧል፡፡ ይህንን እመርታዊ ስኬት ማስመዝገብ የተቻለው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ፤ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በማሻሻል፤ የዜጎችን ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት በማሳደግ፤ የቢዝነስ ሥርዐቱን ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ፤ የኢትዮጵያን የዲፕሎማሲ ዐቅም ከዜጋ ተኮር እና ብሔራዊ ጥቅም አንጻር በመግራት የመደመር መንግሥት ባደረገዉ ሰፊ ጥረት እንደሆነም ነው የተመላከተው።
ኢትዮጵያ የማዕድን ሀብቶቿን በላቀ የኃላፊነት ስሜት በሕጋዊ አግባብ መጠቀም ጀምራለች፤ ታዳሽ ኃይልን በማምረት ከራስ አልፎ ለቀጠናዉ የኃይል ምንጭ ኾናለች፤ ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚን በመተግበር ኹለንተናዊ ዕድገቶችን እያስመዘገበች መጥታለች፤ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በዓለም ገበያ ተወዳድራ የመሸጥ ዐቅም ፈጥራለች።
የመንግሥት የልማት ዕቅድ ከቁጥ ቁጥ ወጥቶ ትውልድን ታሳቢ ያደረገ ግብ አስቀምጦ እየተተገበረ ነው፡፡ በ2018 ዓ/ም በሁሉም መስክ ከተስፋ ብርሃን ወደሚጨበጥ ለውጥ የመሸጋገር ሀገራዊ ራዕይን ማሳካት መቻሉ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ኢትዮጵያን በ2023 ዓ.ም አፍሪካዊት የብለጽግና ተምሳሌት የማድረግ ግብ ተቀምጦ ርብርብ እየተደረገ የስኬቱ ዋዜማ እየተቃረበ ነው።
ኢትዮጵያ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በመደመር መንግሥት በተነደፉ የፖሊሲ ሐሳቦች ኹለንተናዊ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ጉዞን ጀምራለች፡፡በገቢ አሰባሰብ ላይ የታየዉ እመርታ አንዱ አብነት ነው፡፡ የግብር እና ታክስ መሠረትን በማስፋት፣ ገቢ የመሰብሰብ ዐቅምን በማሳደግ፤ የግብር ከፋዩን የመንግሥት አገልግሎት እርካታ በመሶብ አንድ ማእከል እና በዲጂታል አገልግሎቶች ከፍ በማድረግ የላቀ አፈጻጸም ማሳየት ተችሏል፡፡ በዚህም የበጀት ጉድለትን በእጅጉ ማጥበብ መቻሉ ተገልጿል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመንግሥት ፕሮጀክቶችን የመፈጸም ዐቅም በእጅጉ አድጓል፡፡ ፕሮጀክቶች መቼ እንደሚጀመሩ እና በምን ያህል በጀት እንደሚፈጸሙ ብቻ ሳይኾን መቼ ተጠናቅቀው በትክክል አገልግሎት እንደሚሰጡ ጭምር በከፍተኛ የራስ መተማመን የመሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ መናገር የሚቻልበት ቁመና ላይ ተደርሷል፡፡
እመርታዊ ስኬቶችን ዕውቅና ለመስጠት፣ በቀጣዮቹም ዓመታት የበለጠ እመርታዊ ስኬቶችን ለማስመዝገብ መዘጋጀት አስፈላጊ በመኾኑ ዛሬ ጳጒሜን 01 ቀንን “የኢትዮጵያ ማንሰራራት!” በሚል መሪ መልእክት እየተከበረ እንደሚገኝ አገልግሎቱ አስታውቋል።