አርሰናል ከቼልሲ፡ የሳምንቱ ተጠባቂ የሊግ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከቼልሲ፡ የሳምንቱ ተጠባቂ የሊግ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ):- በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት መርሐ ግብር አርሰናል ከቼልሲ ዛሬ የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠባቂ ነው።
የለንደን ደርቢ ጨዋታ ምሽት 12፡30 ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።
አርሰናል እና ቼልሲ በተመሳሳይ በስድስት ነጥብ፣ በግብ ክፍያ ተበላልጠው ሶስተኛና አራተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ባለሜዳው አርሰናል በሁለቱ የሊግ ጨዋታዎች አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ምንም ግብ አላስተናገደም። ይህም የቡድኑን፣ በተለይም የተከላካይ መስመሩን ጥንካሬ የሚያሳይ ነው።
ተጋጣሚው ቼልሲ በሁለት ጨዋታዎች ሰባት ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ አምስት ግቦች ተቆጥረውበታል። ቼልሲ የማጥቃት እንቅስቃሴው ጥሩ የሚባል ቢሆንም በተከላካይ ክፍሉ ላይ ያሉ ድክመቶችን ማረም ይኖርበታል።
ሁለቱ የለንደን ተቀናቃኝ ክለቦች በሊጉ ሲገናኙ የአሁኑ ለ69ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 68 ጨዋታዎች አርሰናል በ28ቱ ድል ሲቀናው፣ ቼልሲ 20 ጊዜ አሸንፏል። በቀሪ 18 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በነዚህ ጨዋታዎች አርሰናል 97 ግቦችን ከመረብ ሲያሳርፍ፣ ቼልሲ በበኩሉ 85 ጎሎችን አስቆጥሯል።
ባለፉት አምስት የሊግ ግንኙነታቸው አርሰናል በሶስቱ ሲያሸንፍ፣ በቀሪዎቹ ሁለት ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። ቼልሲ ለመጨረሻ ጊዜ አርሰናልን በሊጉ ያሸነፈው እ.አ.አ በ2021 ነው።
የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ አርሰናል በአዲሱ የውድድር ዓመት ያደረጋቸውን ሁለት ጨዋታዎች በማሸነፍ ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን በጥሩ ሁኔታ ጀምሯል። ተጋጣሚው ቼልሲም ሁለቱን የሊግ ጨዋታዎች በድል በመወጣት መልካም ጅማሮ አድርጓል። በመሆኑም የሁለቱ የለንደን ክለቦች ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
የ41 ዓመቱ ክሪስ ካቫናግ ተጠባቂውን ፍልሚያ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኤቨርተን ከማንችስተር ዩናይትድ በሂል ዲኪንሰን ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ኤቨርተን ከሁለት ጨዋታዎች ማግኘት የቻለው አንድ ነጥብ ብቻ ሲሆን፣ ተጋጣሚው ማንችስተር ዩናይትድ ሶስት ነጥብ አለው።
ባለሜዳው ኤቨርተን በሊጉ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል። በሁለተኛው ሳምንት ኤፕስዊች ታውንን 5 ለ 2 የረታው ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይፋለማል። ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።