ቀጥታ፡

የግብርና ልማትን ጨምሮ በቱሪዝም ፣ ኢንዱስትሪና የማዕድን ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያን እመርታና ብሩህ ተስፋ የሚያመላክት ነው

ሐረማያ ፤ ጳጉሜን 1/2018 (ኢዜአ) ፦ የግብርና ልማትን ጨምሮ በቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና የማዕድን ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያን እመርታና ብሩህ ተስፋ የሚያመላክት መሆኑን በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሃብት ተባባሪ ፕሮፌሰር ከተማ በቀለ (ዶ/ር) ገለጹ።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሃብት ተባባሪ ፕሮፌሰር ከተማ በቀለ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ብዝሃ የኢኮኖሚ አማራጮች ቀጣይነት ያለው እድገትና ስኬት የሚያመጡ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የግብርና ልማትን ጨምሮ በቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪ፣ የማዕድን ዘርፍ እና በዲጅታላይዜሽን የተከናወኑ ተግባራት የላቀ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን አንስተዋል።

የግብርናው ዘርፍ አገሪቷ ያላትን የሰው ሃይል፣ ውሃ፣ መሬትና ሌሎች ሃብቶችን በአግባቡ በመጠቀም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ የሚታይና የሚጨበጥ ውጤት መገኘቱን ጠቅሰዋል።

በተለይም ደግሞ የስንዴ ልማት በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ የተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጅነት የመውጣት ጥረት በጥሩ መንገድ ላይ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የቱሪዝም፣ የማዕድን እና የአይ ሲቲ ሴክተሮችም ኢትዮጵያን ወደ ፊት እያራመዱ ያሉ ስለመሆናቸው አብራርተዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተለይ ደግሞ በ«ኢትዮጵያ ታመርት» ንቅናቄ በመታገዝ ምርታማነትን በማሳደግ ለወጪ ንግድና ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በመጠቀም ስኬት ስለመመዝገቡ አንስተዋል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልና የቴክኖሎጂ ሽግግር ከማበርከት ባለፈ የውጭ ምንዛሬን በማዳን ረገድ ትርጉም ያለው ውጤት አምጥቷል ብለዋል።

በድምሩ የግብርና ልማትን ጨምሮ በቱሪዝም፣ ኢንዱስትሪና የማዕድን ዘርፎች የተመዘገበው ስኬት የኢትዮጵያን እመርታና ብሩህ ተስፋ የሚያመላክት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም