ቀጥታ፡

የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባን እንገኛለን-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ጳጉሜን 1 /2018 (ኢዜአ)፦የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባን እንገኛለን ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የእመርታ ቀንን በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት፣አባቶቻችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ታላቅ ሀገር አውርሰውናል ብለዋል።

ዛሬ ደግሞ እውነተኛ ሉዓላዊነትን እያረጋገጥን ያለነው ከልመናና ከጥገኝነት በተላቀቀው አዲሱና ታሪካዊው መንገዳችን ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በመልዕክታቸው በሚሊዮን በሚቆጠር ዶላር ስንዴ ከማስገባት ተነስተን ዛሬ የአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች በመሆን የሚሊዮን ዶላሮችን ወጪ ማስቀረት ችለናል ነው ያሉት።

በ "ሌማት ትሩፋት" የምግብ ዋስትናን በተግባር እያረጋገጥን፣ በ "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን።

ከዚህ ቀደም የማይደፈሩና አይነኬ ይባልላቸው የነበሩ ከባድ የማክሮ-ኢኮኖሚ ሪፎርም ውሳኔዎችን በቁርጠኝነት በመተግበር፤ የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባን እንገኛለን በማለት ገልፀዋል።

እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ድሎች ኢትዮጵያ በሚያጋጥሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሸብረክ ሳትል በፅናት መጓዝ መቻሏን የሚያረጋግጡ ህያው ምስክሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህ የእመርታ ጉዟችን ለመጪው ዓመት የሰነቀው ተስፋ እጅግ ግዙፍ ነው ብለዋል።
 
#EthiopiaDelivers

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም