ኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባውን ሊያደርግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባውን ሊያደርግ ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት 74ኛው አስቸኳይ ስብሰባውን መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም በጅቡቲ ያካሂዳል።
በስብሰባው ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እና የኢጋድ አባል ሀገራት ተወካዮች ይሳተፋሉ።
በቀጣናው ሰላም እና ጸጥታ እንዲሁም በሌሎች አበይት ጉዳዮች ላይ ምክክር ይደረጋል።
ይህ ስብሰባ አባል ሀገራት በቀጣናው ያለውን የጸጥታና የደህንነት ሁኔታ እና እየተከናወኑ ያሉ ቀጣናዊ ጥረቶችን በመገምገም ለሰላም፣ መረጋጋትና ትብብር ያላቸውን የጋራ አቋም እንዲያጠናክሩ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የድርጅቱን ተልዕኮ እና በቀጣናው ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ላይ የሚያደርገውን ድጋፍ እና የኢጋድ ስምምነትን (IGAD Treaty) ተፈጻሚነት ማጠናከርን ጨምሮ በዋና ዋና ተቋማዊ ጉዳዮች ላይ ይመክራል።
ስብሰባው የኢጋድ አባል ሀገራት በቀጣናው የሚገኙ ተግዳሮቶችን በጋራ ለመቅረፍ እንዲሁም ለሕዝቦቻቸው ሰላም፣ መረጋጋትና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያረጋግጡበት እንደሆነም ተገልጿል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከኢጋድ ቁልፍ የፖሊሲ አደረጃጀቶች መካከል አንዱ ሲሆን፣ የድርጅቱን ሥራዎች በመምራትና በአባል ሀገራት መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫወት ነው።