ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላጣቻቸው የልማት ዕድሎችና ለደረሰባት ታሪካዊ በደል ማካካሻ የመጠየቅ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት አላት - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዓባይ ውሃ አጠቃቀም ላጣቻቸው የልማት ዕድሎችና ለደረሰባት ታሪካዊ በደል ማካካሻ የመጠየቅ ሕጋዊና ተፈጥሯዊ መብት አላት
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ውሃ አጠቃቀም ላጣቻቸው ሰፊ የልማት ዕድሎች፣ ለደረሰባት ታሪካዊ በደልና ለተፈጸመባት ኢ-ፍትሐዊ ግፍ ተገቢውን ማካካሻ የመጠየቅ ሕጋዊ፣ ተፈጥሯዊና ኢኮኖሚያዊ መብት እንዳላት የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች የቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ገለጹ።
ብርሀኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) የምስራቅ አፍሪካ ፖሊሲ ምርምር ኢንስቲትዩት መስራችና የቀድሞው ምክትል ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች የቀድሞ ሚኒስትር ዴኤታ ናቸው።
ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ ከምታመነጨው ከፍተኛ የውሃ ድርሻ አኳያ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም እንዲሰፍን ስትታገል ቆይታለች።
ኢትዮጵያ ለዓባይ ወንዝ የምታበረክተው ከፍተኛ የውሃ ድርሻና በታሪክ በነበራት ዝቅተኛ የውሃ አጠቃቀም መካከል ያለው አለመጣጣምና ልዩነት የፍትሐዊ ተጠቃሚነት መሰረታዊ ጥያቄን የሚያስነሳ ነው ብለዋል።
በዓባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት የቆየው ኢ-ፍትሐዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ውስንነትም የታሪክ እርማትና ካሳም ጭምር የሚያስፈልገው ሕጋዊና ፍትሐዊ መሰረት ያለው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ከ86 በመቶ በላይ የዓባይ ውሃ ምንጭ ኢትዮጵያ ሆና ሳለ ምንም ሳትጠቀም፣ ግብፅ በአንጻሩ 85 በመቶ የወንዙን የውሃ ሃብት ስትጠቀም ቆይታለች ብለዋል።
በዚህ መነሻነትም ኢትዮጵያ እስካሁን ለደረሰባት ታሪካዊና ኢ-ፍትሐዊ ኪሳራ ግልፅ ማካካሻ የመጠየቅ ሕጋዊና ፍትሐዊ መብት እንዳላት አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በዓባይ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባታል ያሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ የሥነ-ምኅዳር ሚዛን ለመጠበቅ ለምታበረክተው የልማት አስተዋጽኦ ካሳ ያስፈልጋታል ብለዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት ሕጋዊ ካሳ በአረንጓዴ ዐሻራና ሥነ-ምኅዳር ጥበቃ፣ የደን ልማትና ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት በምታበረክተው አስተዋጽኦ ልክ መታየት እንደሚኖርበት አብራርተዋል።
የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራትም ወንዙን ለመጠበቅ ኢትዮጵያ የምታደርጋቸውን ሁለንተናዊ የአረንጓዴ ልማት የመደገፍ ግዴታ ጭምር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ ዓባይን ባለመጠቀሟ ብዙ የልማት ዕድል አምልጧታል ያሉት ብርሃኑ (ዶ/ር)፤ ይህም ሳይበቃ ግብፅ ወንዙን በብቸኝነት ከመጠቀም ባሻገር የኢትዮጵያ የግጭቶች ምንጭ ሆና ዘልቃለች ብለዋል።
ግብፅ በጫካ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂና የሽብር ኃይሎችን በቁሳቁስ በመደገፍ ኢትዮጵያ በውክልና ጦርነት እንድትቆይ በማድረግ የባሕር መግቢያና መውጫ በሯን ጭምር እንዳሳጣቻት አስታውሰዋል።
በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከልም ሳይንሳዊ፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም የትብብር ምኅዳርን የሚያጎለብት ጥናቶችን ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል።
የዓባይ ወንዝ የትብብር የወደፊት አቅጣጫ የውሃ መጠንን ከመከፋፈል ባሻገር የወንዙ ሥርዓት የሚፈጥራቸውን ጥቅሞች በፍትሐዊነትና በመጋራት ላይ መመሥረት እንዳለበት አመላክተዋል።