የቡና ወጪ ንግድ እድገት - የኢትዮጵያ እመርታ አንዱ ማሳያ - ኢዜአ አማርኛ
የቡና ወጪ ንግድ እድገት - የኢትዮጵያ እመርታ አንዱ ማሳያ
ገና ወደ ውስጥ ሲገቡ ለምለም ቄጠማ በተጎዘጎዘበት ቤት እና ትኩስ በተቆላ ቡና ከደማቅ ፈገግታ ጋር አቀባበል ታደርጋለች። የቡናው ሽታ ደግሞ ልዩ መዐዛ አለው። አለምነሽ ሀብቱ ወደ ከተማ ከገባች በኋላ ድሮም የምትወደውን ቡና የሰርክ ስራዋ የእለት መተዳደሪያዋ አድርጋዋለች።
ቡና ትወዳለች የአዘገጃጀት ድምቀቷንም ሌሎች ይወዱላታል። እሷ የምታዘጋጀውን የጀበና ቡና ለመጠጣት የመጣ ደንበኛዋ አትርፎ እንደወጣ እንዲሰማው የማድረግ ተሰጥኦ አላት። ቡና ትወዳለች ትጠጣለች ታጠጣለች ። እንደሷ ሁሉ ቡና ለኛ ለኢትዮጵያውያን አብሮን የሚውል፣ የሚያመሽ በብዙዎቻችን ቤት በቋሚነት የማይጠፋ ማህበራዊ መገናኛችን መመካከሪያችንም ጭምር ነው።
በቡና ምርት በርካታ መሬትን ሸፍና ብዙ አርሶ አደሮችን እያሳተፈች የወጪ ንግዷን ለማሳደግ የምትጥረው ኢትዮጵያ ደግሞ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የምታገኝበት ዋንኛ የግብርና ኢኮኖሚው የጀርባ አጥንትም ነው።
ባለፉት ዓመታት የቡና ምርትና ምርታማነት በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ የሀገሪቱን የወጪ ንግድ ድርሻም እያሳደገ መምጣቱን የተለያዩ መረጃዎች እያሳዩ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄ ማብራሪያ ሲሰጡ ለቡና ልማት የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን በአለም ሶስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን ማንሳታቸው ይታወሳል።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከቡና ወጪ ንግድ የተገኘው ከ3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ኢትዮጵያ በበጀት ዓመቱ ወደ ውጭ ከላከቻቸው ምርቶች ከፍተኛው እንደነበረም አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ከብራዚልና ከኮሎምቢያ በመቀጠል በዓለም 3ኛዋ ትልቋ የቡና ላኪ ሀገር መሆኗን እና በአፍሪካም ቀዳሚ ደረጃ ላይ መቀመጧን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን የሀገር ውስጥ የቡና ፍጆታ ከመቻል አልፈን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የመጣው ለውጥ የሀገራዊ የሪፎርሙ ስኬት መገለጫ ነው ማለታቸውም ይታወሳል።
ይህ የአንድ ዓመት ምርት እንግዲህ ኢትዮጵያ ባለፉት 17 አመታት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ካገኘችው 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ጠቅላላ ገቢ ጋር ሲነጻጸር አስደማሚ ስኬት መሆኑ አያጠራጥርም።
አረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ለቡና ኤክስፖርት እድገት ስኬት አስተዋጽኦ ማበርከቱን በወቅቱ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ
ቡናን ካልተከልን ፤ ካልተንከባከብን ፤ካልለቀምን፤ ካላጠብን፤ካላሸግንና ካላጓጓዝን ይህ ውጤት ሊመጣ አይችልም ብለውም ነበር።
ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና መገኛ እንደመሆኗ የምርቱን እድገትና ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተፈላጊነቱን ለማሳደግ እየተከናወኑ ባሉ ተከታታይ ስራዎች ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል።
ባለፉት ተከታታይ ዓመታት የተከናወነ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር በሌሎች ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊና የተፈጥሮ ሥነ-ምህዳራዊ ግዙፍ አበርክቶው እንዳለ ሆኖ በቡና ምርት እድገት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
ለዚህ ማሳያው ደግሞ መርሃ-ግብሩ ሲጀመር በ2011 ዓ.ም. ስድስት መቶ ሺህ ችግኝ የተተከለ ሲሆን ዓመታዊ ምርቱም 5 መቶ ሺህ ሜትሪክ ቶን ነበረ። በወቅቱ የተገኘው የውጭ ምንዛሪም 738 ሚሊዮን ዶላር ነበር።
ይሄ ትኩረት በመቀጠሉም የቡና ችግኝ የመትከሉ ስራ አድጎ በ2017 ዓ.ም. ላይ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን የደረሰ ሲሆን በዛው ዓመት 2 ነጥብ 65 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ተችሏል። ከላይ እንደተገለጸው የ2018 የቡና ወጪ ንግድ ገቢ 3 ነጥብ 1 መድረሱ ለዘርፉ የተሰጠውን ትኩረት እና የተመዘገበውን እመርታ የሚያሳይ ነው።
ለዓመታት በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የቆየው የቡና ወጪ ንግድ ገቢ በአጭር ጊዜ መለወጥ እና ኢትዮጵያ ወደ ተለያዩ ሃገራት ከምትልካቸው የግብርና ምርቶች ከፍተኛውን ድርሻ ይዞ መቀጠሉ ለዘርፉ ለተሰጠው ትኩረት እና ለተገኘው ውጤት አንዱ መገለጫም ነው።
የኢትዮጵያ ቡና በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊነቱ በየጊዜው እየጨመረም ይገኛል። ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጃፓን፣ ቤልጂየም እና ደቡብ ኮሪያ ከቀዳሚዎቹ የኢትዮጵያ ቡና ገዢዎች መካከል የሚጠቀሱ ሲሆን በቻይና እና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት የቡና ፍጆታና የመጠጣት ባህል በፍጥነት ማደጉ ለኢትዮጵያ አዳዲስ የገበያ እድሎችን ፈጥሯል።
ይህ የኢትዮጵያ የእመርታ ጉዞ በቀጣይም ተጠናክሮ የሚቀጥል ብልጽግናዋንም የምታረጋግጥ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላትና የበለጠ ጠንካራ ሀገርነቷን የምታስቀጥልበት አዲስ ምዕራፍም ነው።