ቀጥታ፡

ከጥገኝነት ወደ ራስን መቻል - የኢትዮጵያ ታምርት የኢኮኖሚ እመርታ

(በሙሴ መለሰ)

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሽግግር ጉዞ ውስጥ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ መዋቅራዊ ማነቆዎችን ለመፍታት፣ ምርታማነትን ለማሳደግ እና የሀገር ውስጥ ምርትን ለማዘመን የታለመ ታላቅ ሀገራዊ መርሐ ግብር ነው።

ይህ ሀገራዊ ንቅናቄ በአጭር ዓመታት ውስጥ በኢኮኖሚ ደህንነት ግንባታ፣ የውጭ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት እና በሰፊው የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሁለንተናዊ እመርታ አምጥቷል።

መርሃ ግብሩ በይፋ የተጀመረው በመጋቢት ወር 2014 .. በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አማካኝነት ሲሆን፣ አጀማመሩ ለዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሯል።

የአገር ውስጥ ምርትን ማሳደግ የማኑፋክቸሪንግ አቅምን ሙሉ በሙሉ በመጠቀም የምርት መጠንና ጥራትን ማሳደግ፣ ቀደም ሲል ከውጭ አገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርቶች መተካት ፣ጥራታቸውን የጠበቁ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ማሳደግ ፣ የስራ ዕድል መፍጠር እና በዘርፉ ያሉ ማነቆዎችን መፍታትም ዓላማው ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አምራች ዘርፉን ማሳደግ የፖሊሲ ምርጫ ሳይሆን የሀገርን የኢኮኖሚ ነጻነት የማስከበር ዋነኛ ጉዳይ መሆኑን በተደጋጋሚ ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ላይ አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ዘርፉን በባለቤትነት የሚመራ፣ የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን የሚያቀል እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያረጋግጥ የአምራች ኢንዱስትሪዎች ካውንስል መቋቋሙ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ቅንጅት እንዲጠናከር አድርጓል።

ከዚህ ጎን ለጎን የግሉ ዘርፍ አምራቾች በንቅናቄው ውስጥ በንቃት እንዲሳተፉ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች በመፈጠሩም፣ የሕዝብና የግል አጋርነት እጅግ እየጎለበተ መጥቷል።

የምርት ማስተዋወቅና የገበያ ትስስር ለመፍጠር 2015 . አንስቶ ሀገር አቀፍ የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖዎች በመካሄድ ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ በርካታ አምራቾች ተሳትፈው በቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር የገበያ ትስስር ውል ተፈጽሟል።

ንቅናቄው ከተጀመረ ወዲህ ተዘግተው የነበሩ ከአንድ ሺህ በላይ ፋብሪካዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ የተመለሱ ሲሆን፣ እጅግ ብዙ አዳዲስ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ግዙፍ ፋብሪካዎችም ወደ ምርት ገብተዋል።

ይህ ሁሉ አበረታች ርብርብ የኢንዱስትሪዎችን አማካይ የማምረት አቅም 67 በመቶ በላይ እንዲሻገር ያስቻለ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ አምራቾች የምርት ድርሻም 30 በመቶ ወደ 45 በመቶ ከፍ በማለት አስደናቂ እምርታ አሳይቷል።

በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግና አዳዲስ ባለሀብቶችን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለመሳብ በተደረጉ ጥረቶችም ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ተደርጓል።

የኢንቨስትመንት ፍሰትን ይበልጥ ለማሳለጥ እና አላስፈላጊ ቢሮክራሲን ለማስወገድ የሚያስችሉ አዳዲስ አሰራሮች በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ተግባራዊ መደረግ ጀምረዋል።

በቴክኒክና ሎጅስቲክስ ድጋፎች የታገዘው የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኢንስቲትዩት እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ርብርብ የሀገር ውስጥ ምርቶች ጥራትና ተወዳዳሪነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲያድግ አስችሏል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና ዲጂታል አሰራሮችን በማስተዋወቅ ረገድ ፋብሪካዎች በዘመናዊ አሰራር እንዲመሩ የማድረግ ስራዎች በመሰራታቸው የምርት ጥራትና ፍጥነት በከፍተኛ ደረጃ እየተሻሻለ ነው።

ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች የሚሆን የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የቴክኖሎጂ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎችን የማፍራት ሥራ በስፋት እየተከናወነ ይገኛል።

ከፋይናንስና ከምርት ዕድገት ባሻገር፣ ንቅናቄው ለብዙ ወጣቶችና ሴቶች ዘላቂ የሥራ ዕድል የፈጠረ ሲሆን፣ በዘርፉ ሰፊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እመርታ እየተመዘገበ ይገኛል።

2018 . በጀት ዓመት የኢንዱስትሪ ምርቶችን እና የግብርና ማቀነባበሪያ ግብዓቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት 5 ነጥብ9 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገመት የውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለ ሲሆን፣ በገበያ ትስስሮችም ከፍተኛ ውሎች ተፈጽመዋል።

የሀገር ውስጥ አምራቾች ወደ ውጭ ገበያ ያላቸውን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችሉ ዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ምስክር ወረቀቶችን እንዲወስዱ ሰፊ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሀገር አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት (ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት) የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ጭማሪ እንዲያሳይ በማድረግ ረገድ ትልቅ እመርታ ታይቷል።

ለአምራች ኢንዱስትሪዎች አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የኢንዱስትሪ መንደሮችና የረጅም ጊዜ ብድር ማመቻቸት ላይ የመንግስት ትኩረት የተደረገ ሲሆን፣ ይህም ለቀጣይ ዕድገት ትልቅ መሠረት ነው።

ለመንግስት ሰራተኞች የሚቀርቡ አልባሳት፣ ደብተሮችና የቢሮ ቁሳቁሶች መቶ በመቶ ከሀገር ውስጥ አምራቾች እንዲገዙ የሚያስገድደው አሰራር ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ገበያም እየተጠናከረ መጥቷል።

ምርቶችን በአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ገበያ ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ የወደፊቱ ዋና አቅጣጫ በመሆኑ፣ አምራቾች ዝግጅታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ  ከውጭ ጥገኝነት ተላቆ በራስ አቅም የማምረት ታሪካዊ እመርታን ያመጣ ታላቅ የኢኮኖሚ አብዮት ሲሆን ይህም ኢትዮጵያን የአፍሪካ ቀዳሚ የኢንዱስትሪና የማኑፋክቸሪንግ ማዕከል ለማድረግ ያስችላታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም