ቀጥታ፡

የወረዳው ህዝብ በልማት እያሳየ ያለው ተሳትፎ ለሌሎች ምሳሌ የሚሆን ነው - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

አርባምንጭ ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ) በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን የመሎ ኮዛ ወረዳ ህዝብ በልማት ያለው ተሳትፎ ለሌሎች ምሳሌ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ አስታወቁ።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጎፋ ዞን የመሎ ኮዛ ወረዳ ህዝብ ባዋጣው ከ343 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ 11 የተለያዩ የልማት ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን ዛሬ ስራ አስጀምረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደገለጹት በክልሉ ግብርናን በማዘመን የህዝቡን የኢኮኖሚ ሉዐላዊነት ለማረጋገጥ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው።

በመሎ ኮዛ ወረዳ በህዝብ ትብብር የተገዙ ማሽኖች የወረዳው ህዝብ የኢኮኖሚ ሉዐላዊነት እንዲያረጋግጥ ጉልህ ፋይዳ ያላቸው መሆኑን ጠቅሰዋል።

የወረዳው ህዝብ በልማት ያለው ተሳትፎ ለሌሎች ምሳሌ እንደሚሆን አስታውቀዋል።

አመራሩ ህዝቡ ያሳየውን አንድነትና አብሮነት ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።


 

የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር ዳግማዊ አየለ በበኩላቸው በዞኑ የሚገኙ የተፈጥሮ ፀጋዎችን በመጠቀም ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ከህዝብ ጋር በቅንጅት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

የመሎ ኮዛ ወረዳ ህዝብ የይቻላል መንፈስ በመላበስ ያሳየው ትብብር፣ አንድነትና ቁጭት ለሌሎች በአርአያነት የሚጠቀስ ነው ብለዋል።

የተገዙ ማሽኖችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ዞኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

የመሎ ኮዛ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ሙሉነህ አውሳቶ እና የላሃ ከተማ ከንቲባ አሸናፊ ጮራ አካባቢው የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ የቡና፣ የኮረሪማ፣ ማሾ፣ የሰሊጥና ሌሎች ሰብሎች በስፋት የሚመረትበት መሆኑን ጠቁመዋል።

በወረዳው ያለውን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል ለመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው ለተግባራዊነቱም የህዝቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።


 

በዚህም በህዝብ ትብብር ከ343 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ሶስት ለመንገድ ስራ የሚያገለግሉ ማሽኖች፣ አምስት ትራክተሮች፣ ሁለት ሲኖትራክና አንድ አይሱዙ ተሽከርካሪዎች ግዥ መፈጸሙን ጠቅሰዋል።

በስነ ስርአቱ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ የጎፋ ዞን፣ የመሎ ኮዛ ወረዳና የላሃ ከተማ አስተዳደር አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም