ቀጥታ፡

የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የውሃ ተደራሽነት በማስፋት ተጠቃሚ እየሆነ ነው

ሰመራ፤ ነሀሴ 30/2018 (ኢዜአ)፦ የአርብቶ አደር አካባቢዎችን የውሃ ተደራሽነት በማስፋት ተጠቃሚነቱን ማሳደግ መቻሉን የአፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ።

ቢሮው በገቢ ረሱ ዞን በሚገኙ ሶስት ወረዳዎች ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ሶስት የውሃ ፕሮጀክቶችን በዛሬው ዕለት አስመርቋል።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ አህመድ ሻሚ እንዳሉት፣ በክልሉ ለውሃ አገልግሎት ተደራሽነት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።


 

በዚህም አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የሚገኝባቸውን የተለያዩ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ ተጠቃሚነትን ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

ከ120 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን ጥያቄ ለመመለስና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ገልፀዋል።

በአሚበራ፣ ሃሩካና ገለአሎ ወረዳዎች የተገነቡት የውሃ ፕሮጀክቶች ከ20 ሺህ በላይ አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደረጉ ናቸው ብለዋል።

የገቢ ረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን መሐመድ በበኩላቸው፣ የፕሮጀክቶቹ ሥራ መጀመር አርብቶ አደሩ ለቤት እንስሳቱ ጭምር ውሃ ለመፈለግ የሚያጠፋውን ጊዜና ጉልበት የሚያስቀር ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የአካባቢው ማህበረሰብ በተደጋጋሚ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም