ነገን ተልሞ ለትውልድ መቅረጽ የመደመር መንግሥት መገለጫው ሆኗል። - ኢዜአ አማርኛ
ነገን ተልሞ ለትውልድ መቅረጽ የመደመር መንግሥት መገለጫው ሆኗል።
የመደመር መንግሥት ለትውልድ የሚሻገር አገራዊ ወረት እያኖረ፤ በተጨባጭ ውጤቶችም እየተገለጸ ቀጥሏል። ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከባንዳ እስከ ባዳ በቅንጅት የተወረወሩበትን እያንዳንዷን ጠጠር በጥበብና በጽናት እየለቀመ የአገር ግንባታ ጡብ አድርጓቸዋል፤ ከጸኑ ፈተናዎች የሰሉ ዕድሎች ተፈልቅቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ “ኢትዮጵያዊ ጽናት እና አርቆ አስተዋይነት የታየበት” ሲሉ ያረጋገጡት እና መንግሥት ይፋ ያደረጋቸው የጉባ ብስራቶች የሀገራችን እምቅ አቅም በተግባር የሚገለጥባቸው ግዙፍ ማሳያዎች ናቸው። ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚፈጀው ይህ ማዕቀፍ የኢትዮጵያን የነገ ዕጣ ፈንታ በሰፊው የሚቀይር ታሪካዊ የጋራ ስኬት ነው።
ለመደመር መንግሥት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የብልጽግናው ዋና መለኪያ ነው። የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ መጀመሩ የአርሶ አደራችንን ምርታማነት በብዙ እጥፍ ያሳድጋል። እንደ ሀገርም በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላርን እናተርፍበታለን።
በአፍሪካ ግዙፉ የሆነው አዲሱ የቢሾፍቱ አየር ማረፊያ ግንባታም እውን እየሆነ ነው። ይህ ፕሮጀክት ኢትዮጵያን የአህጉሪቱ ዋንኛ የሎጂስቲክስ፣ የንግድ እና የዲፕሎማሲ መገናኛ በማድረግ የጂኦ-ኢኮኖሚ አቅማችንን ወደ ታላቅ ከፍታ ያሸጋግረዋል። ብዙዎች በሀገራቸው እውን እንዲሆን የሚመኙትን ይህን ታላቅ ፕሮጀክት ኢትዮጵያውያን በጽናት ጀምረነዋል፤ እንፈጽመዋለን።
የመደመር መንግሥት የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የነገው ትውልድ ዕድል የሚቀየር ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን በአጽኖት ተልሟል። የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነት ያለ ኢነርጂ ሉዓላዊነት የሚታሰብ አይደለም። ለዚህም ነው መንግሥት የኢነርጂ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ የኢኮኖሚ ነጻነታችን ማዕዘን ድንጋይ ነው በሚል ስትራቴጂያዊ ትኩረት የሰጠው።
ከታላቁ የህዳሴ ግድባችን ቀጥሎ የኢትዮጵያ ማንሰራራት ምልክት የሆነው የመጀመሪያው የጋዝ ፋብሪካችን ተመርቋል፤ ሁለተኛውም እየተገነባ ነው። የነዚህና ሌሎች በሂደት ላይ ያሉ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ እና ሥራ መጀመር ከውጭ የሚገባውን የኢነርጂ ፍላጎት በማሟላት ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ያስቀራል፤ ለኢንዱስትሪ ዘርፉ ማበብም ጽኑ መሠረት ይጥላል።
የልማት እውነተኛ ልክ የዜጎች ክብርና ማኅበራዊ ፍትህ መረጋገጥ ነው። መንግሥት ለዚህ አብላጫ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። በመላው ሀገሪቱ የሚከናወነው የ1.5 ሚሊዮን ቤቶች ግንባታ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተጀምሯል። ፕሮጀክቱ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሚሊዮኖችን የቤት ባለቤት ያደርጋል። የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ማኅበራዊ ፍትህን ያረጋግጣል።
መደመር ማለት አብሮ ማደግ እና ሀብትን መጋራት ማለት ነው። እነዚህ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለሚሊዮን ወጣቶች ቀጥተኛ እና ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራሉ። በዚህ ረገድ ገና ከጅምሩ ውጤቶች መመዝገብ ጀምረዋል።
የመደመር መንግሥት ለትውልድ የሚያሻግረው ዕዳን ሳይሆን ምንዳን ነው። አዲሱን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፤ ነገን ዛሬ ተልሞ ለትውልድ መቅረጽ የመደመር መንግሥት ልዩ መገለጫ ሆኗል። ወገባችንን አስረን፣ መቀነታችንን አጥብቀን በላባችን ወዝ የምናኖራቸው ወረቶች ለነገው ትውልድ የሚቀሩ የብልጽግና ውርስ ይሆናሉ። በላባችን ጥረት ኢትዮጵያን በጸና መሠረት ላይ እናቆማለን።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት