ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የህልውና አጀንዳ ነው - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከቀይ ባሕር ጋር የማይነጣጠል ታሪካዊ ቁርኝት ያላትና የባሕር በር ጥያቄዋም የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የህልውና አጀንዳ መሆኑን ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።

አንጋፋው ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፥ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ከጥንት ጀምሮ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ግዛት ወሰን አካል ሆኖ መኖሩን አውስተዋል።

ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎችም የራሳቸውን መገበያያ ገንዘብ በመጠቀም በቀይ ባሕር በኩል እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ይነግዱ እንደነበር አውስተዋል።

ከ1950ዎቹ በኋላም አሰብና ምፅዋ የኢትዮጵያ ዋና የባሕር በር ወደቦች ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰዋል።

ሆኖም የኢህአዴግ መንግሥት ምንም ዓይነት ህጋዊ መሰረት በሌለው ሁኔታ፣ ያለምንም የሕዝብ ውይይትና ያለ በቂ ጥናት በድንገተኛ ውሳኔ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ ማድረጉንም አብራርተዋል።

ለሀገርና ለሕዝብ ኃላፊነት በማይሰማው መንግሥት የተፈጸመው ይህ የጥፋት ውሳኔ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ጠባሳ መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በባሕር ንግድ በተሳሰረች ዓለም ውስጥ 130 ሚሊዮን ሕዝብን ይዞ ያለ ምንም የባሕር መውጫ ረጅም ጉዞ ማሰብ አይቻልም ነው ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ።

የባሕር በር ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በቁጭት የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፥ አሁን ያለው መንግሥት ኃላፊነት የሚሰማው በመሆኑ የባሕር በር አጀንዳን ፊት ለፊት ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።

የባሕር በር ለንግድ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከጥቃት ለመከላከልም ወሳኝ የብሔራዊ ደህንነት ዓምድ ነው ብለዋል።

አክለውም የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድና የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ጠቅሰው፣ ጉዳዩ ትውልድ የማይተወው የህልውና አጀንዳ መሆኑን በአፅንኦት ተናግረዋል።

በቀይ ባሕር ዙሪያ ያሉ ሀገራት የሕዝብ ብዛትና ኢኮኖሚ ተደምሮ የኢትዮጵያን ግማሽ አቅም እንኳ እንደማይደርስ የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መምጣት ለእነዚህ ሀገራትም ትሩፋት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ቀጣናው የኃያላን ሀገራት መራኮቻና የተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሰለባ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ አኳያ የቀጣናው ሀገራት በጋራ መልማት የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረዋል ።

የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት በመቀነስ በኢኮኖሚና በታሪክ የተሳሰረውን ሕዝባቸውን ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ በአካባቢው ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ መሆኗ ፋይዳው ድንበር ዘለል ነው ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ፥ ከባሕር በር ተነጥላ ልትኖር ስለማትችል የአካባቢው ሀገራት የመውጫ በር ሊሰጧት ይገባል ነው ያሉት።

ይህ ካልሆነ ግን ግዙፍ የህዝብ ቁጥር ያላት በመሆኗ በጊዜ ሂደት በተፈጥሯዊ መንገድ የታፈነው ጥያቄ መፈንዳቱ አይቀሬ ነው ብለዋል።

ይህ እንዳይሆን የቀጣናው ሀገራት በሰላማዊ መንገድ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት በመከላከልና ሀብትን በጋራ በመጠቀም መርህ ለኢትዮጵያ የባሕር በር በማመቻቸት የጋራ ህልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም