ቀጥታ፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኢንዱስትሪ ዘርፍ በመጣው ለውጥ በርካታ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል

ወላይታ ሶዶ፤ ነሐሴ 30/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኢንዱስትሪ ዘርፍ በተመዘገበው ስኬት በርካታ ዜጎች የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን "የተቀናጀ የኢንዱስትሪ ልህቀት፣ ለከፍተኛ ምርታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ኤግዚቢሽንና ባዛር በወላይታ ሶዶ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማነቃቃት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል።

በተለይም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል።


 

በማዕከላት የገቡ መካከለኛና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ምርታማነታቸው ከማደጉ ባለፈ ለበርካታ ዜጎች ጊዜያዊና ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቅሰዋል።

ባዛርና ኤግዚቢሽኑም አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ ከማድረግ ባሻገር የገበያ ትስስር በመፍጠር የጎላ ሚና እንዳለው አስታውቀዋል።

በዘርፉ የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በትኩረት እንደሚሰራም እንዲሁ።


 

ኮርፖሬሽኑ የፋይናንስ አቅሙን በማጎልበት፣ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማጠናከርና የኢንቨስትመንት ምህዳሩን በማስፋት ረገድ ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበ ይገኛል ያሉት ደግሞ የክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ጥላሁን ብርሃኑ (ኢ/ር) ናቸው።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 11 አልሚ ባለሀብቶች ወደ ሥራ መግባታቸውንና ከ4 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም