ቀጥታ፡

ኢትዮ - ቴሌኮም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮ-ቴሌኮም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገውን በጎተግባር አጠናክሮ እንደሚቀጥል የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ።

ኢትዮ - ቴሌኮም 25ኛ ዓመቱን ለያዘው "ስለ እናት" በጎ አድራጎት ድርጅት የ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር የገንዘብና ዓለምገና ለሚገኘው ውህደት ቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ደግሞ የተማሪ መማሪያ ደብተር ለግሷል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ የኩባንያውን ድጋፍ በ"ስለ እናት" በጎ አድራጎት ድርጅት እና ውህደት ቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተገኝተው አበርክተዋል።


 

ዋና ስራ አስፈፃሚዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኩባንያው ከመደበኛ ሥራዎቹ ባሻገር የሰዎችን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል።

በአዲስ አበባ የተካሄደው የበጎ አድራጎት ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት መርሃ ግብርም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ የሚደርስ ድጋፍ የሚካሄድበት መሆኑን ገልጸዋል።

ከሃምሳ በላይ የበጎ አድራጎት ተቋማት ጋር በተፈጠረው በትብብር የመስራት ሁኔታም ከ22 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሀገራዊ ለውጡ ማግስት የሚከናወኑ ሰው ተኮር የድጋፍ ሥራዎችን ታሳቢ በማድረግም በስምንት ዓመታት ውስጥ ማህበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ያስቻሉ ድጋፎች መደረጋቸውን አስረድተዋል።

ዘንድሮም በአዲስ አበባ ለ"ስለ እናት" በጎ አድራጎት ድርጅት እና ዓለምገና ለሚገኘው ውህደት ቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

የ"ስለ እናት" በጎ አድራጎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ያሬድ አብዱ በበኩላቸው፤ ኢትዮ ቴሌኮም ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምሮ በተከታታይ እያደረገላቸው ለሚገኘው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ሌሎች ተቋማትም የኢትዮ-ቴሌኮምን የሰብዓዊ ድጋፍ አርዓያነት በመከተል ሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ለውህደት ቅድመ አንደኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ባበረከቱበት ወቅት፤ የትምህርት ተቋማት በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ መፍጠሪያ ማዕከላት ናቸው ብለዋል።

ለዚህም በዘንድሮው ማህበራዊ ኃላፊነትን የመወጣት ተግባር በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ100 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የሚውል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የደብተር ድጋፍ መሰራጨቱን አስታውቀዋል።

የውህደት ቅድመ አንደኛና መደበኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መስራችና የአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አበበ የኋላወርቅ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮ-ቴሌኮም ለትምህርት ቤቱ ላበረከተው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም