መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሠራርን በመቀነስ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ አስችሏል - ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሠራርን በመቀነስ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ አስችሏል - ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
ጎንደር፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ብልሹ አሠራርን በመቀነስ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
ርዕሰ መሥተዳድሩ አረጋ ከበደ የጎንደር መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ዛሬ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
ርዕሰ መሥተዳድሩ በዚሁ ወቅት መሶብ የአንድ ማዕከል የመንግሥት የአገልግሎት አሠጣጥ ሪፎርም አካል በመሆን ዘልማዳዊ እና እንግልት የበዛበትን አሠራር እየቀየረ ነው ብለዋል።
የመንግሥት ተቋማት የሚሰጡትን አገልግሎት በአንድ ማዕከል በማሠባሠብ፣ በማደራጀት፣ ዲጂታል በማድረግ፣ ብልሹ አሠራርን በመቀነስ የተገልጋዮችን እርካታ ለማሻሻል እያገዘ መሆኑንም አስረድተዋል።
በክልሉ ስድስት መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን ተገልጋይን መሠረት ያደረገ በመሆኑ የነበረውን እንግልት የበዛበት አሠራር ሁለንተናዊ በሆነ መንገድ እየቀረ መሆኑን አንስተዋል።
የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተሻለ ተደራሽነትን፣ የላቀ ቅልጥፍናን፣ ግልጽነትን እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጥ መኾኑንም አንስተዋል።
አገልግሎቱ የመንግሥት ተቋማትን በማቀናጀት፣ የእርስ በእርስ የመረጃ ልውውጣቸውን በማቀላጠፍ ለደንበኞች እርካታ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የጎንደር መሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ሕንጻ የከተማዋን ቀደምት የኪነ- ሕንጻ ጥበብ በጠበቀ መንገድ በጥራት ተገንብቶ የተጠናቀቀ መሆኑንም አብራርተዋል።
በቀጣይም በኮምቦልቻ፣ በደብረ ማርቆስ እና ደብረ ብርሃን ከተሞች የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ስራ እንደሚጀምሩም ነው የተናገሩት።
በ2019 በጀት ዓመትም በክልሉ ሁሉም ወረዳዎች እና ከተሞች የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎትን የማስፋፋት ስራ እንደሚሠራም አመላክተዋል።