በነቀምቴ ከተማ ከ 21 ሺህ 800 በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ - ኢዜአ አማርኛ
በነቀምቴ ከተማ ከ 21 ሺህ 800 በላይ ወጣቶች የስራ እድል ተጠቃሚ ይሆናሉ
ነቀምቴ ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ) ፦ በነቀምቴ ከተማ በ2019 በጀት ዓመት 21 ሺ 840 ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የከተማው የስራ እድል ፈጠራ እና ክህሎት ፅህፈት ቤት ገለጸ።
የነቀምቴ ከተማ የሥራ ዕድል ፈጠራና ክህሎት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ አሰፋ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ14 ሺሕ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ የሙያ መስኮች በማሰማራትተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
ከብድር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ወጣቶች የተመቻቸላቸውን የሥራ ዕድል እንዲጠቀሙ በተደረገው ጥረትም በበጀት ዓመቱ 289 ሚሊዮን ብር ብድር መመቻቸቱን ጠቁመዋል።
በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ ወጣቶች የተበደሩትን ገንዘብ በየጊዜው እንዲመልሱ ለማስቻል ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ ከ88 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መመለስ መቻሉንም ገልጸዋል።
በ2019 የበጀት አመትም የወጣቶችን የሥራ እድል ፈጠራ ለማስፋፋት፣ የፋይናንስ ተደራሽነትን ለማሳደግ እና የወጣቶችን ተሳትፎ ለማጠናከር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ነው አቶ ብርሃኑ የገለጹት።
የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ባህላቸውን በማሳደግ በሀገር ግንባታ የበኩላቸውን አሻራ እንዲያኖሩም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው በተለያዩ ዘርፎች 21 ሺሕ 840 ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።
የስራ እድል እየተመቻቸላቸው ያሉ ወጣቶች እንደተናገሩትም የከተማው አስተዳደር ለወጣቶች የሰጠው ትኩረት አስደሳች መሆኑን ገልጸው፤ በስራ እድሉ ተጠቅመው ራሳቸውን እንደሚለውጡ ተናግረዋል።
ወጣት ሙሉጌታ ተስፋዬ፣ በተገኘልኝ የብድር ድጋፍ አነስተኛ የእንስሳት ማድለብ ሥራ ጀምሬያለሁ ብሏል።
ዛሬ ለራሴ ገቢ ከመፍጠር ባሻገር ለሌሎች ወጣቶችም የሥራ ዕድል ፈጥሬያለሁ ብሏል።
ወጣት ሀና አሰጠው በበኩሏ፣ በተሰጠኝ የሙያ ሥልጠናና የፋይናንስ ድጋፍ የልብስ ስፌት ሥራ ጀምሬ በመስራት ቤተሰቤን እየደገፍኩ ነው ብላለች።
የተፈጠረልን ዕድል ለብዙ ወጣቶች ተስፋ ሆኗል ያለችው ወጣቷ በዚህ የስራ እድል መጠቀም ይገባናል ብላለች።