የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመረዳዳት እሴት እንዲጎለብት እያደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን - ኢዜአ አማርኛ
የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመረዳዳት እሴት እንዲጎለብት እያደረገ ነው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን
አሶሳ፤ ነሐሴ 30/2018 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል የመረዳዳት እሴት እንዲጎለብት እያደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ቡልድግሉ ወረዳ ለአቅመ ደካሞች የማዕድ ማጋራት እና የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በማቃለል የመረዳዳት እሴት እንዲጎለብት እያደረገ ነው።
በክልሉ በክረምት ወራት ከበጎ ፍቃደኞች በተጨማሪ የክልሉ የመንግስት ተቋማት በበጎ ፍቃድ አገልግሎት እያደረጉት ያለውን ተሳትፎ አጠናክረው መቀጠላቸውን ገልጸዋል።
በዘንድሮው ክረምት ከ200 በላይ አዳዲስ የቤት ግንባታዎች እና ከ50 በላይ የሚሆኑ የአቅመ ደካሞች ቤቶችን ለመጠገን ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤትም በቡልድግሉ ወረዳ አምስት የአቅመ ደካሞች ቤቶችን እያስገነባ እንደሚገኝ ገልጸው፥ በየደረጃው የሚገኙ መዋቅሮች የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት የስራ አፈጻጸም በየጊዜው በመገምገም ውጤታማ ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ወቅቱ የትምህርት ዘመን የሚጀመርበት በመሆኑ ለተማሪዎች የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በሰዓቱ ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ የሚያደርግና የወላጆችን ጫና የሚቀንስ መሆኑን ገልጸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወረዳው 200 ለሚሆኑ ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ላላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ዱቄት፣ ዘይት፣ ስኳር እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን ለ200 ተማሪዎች ደግሞ የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።